የፍካት ዳግም ፍካት በቅኔ ጳጉሜን! - ኢዜአ አማርኛ
የፍካት ዳግም ፍካት በቅኔ ጳጉሜን!
ጷጉሜ 5/2011 የፍካት ዳግም ፍካት በቅኔ ጳጉሜን! የቀድሞዋ የፍካት ስነ ጽሁፍ ክበብ አባለዓት ከ20 ዓመታት በኋላ 'ዝክረ ጳጉሜን በቅኔ' በሚል መድረክ ዳግም ተገናኝተዋል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ባወጣው የኪነ ጥበብ ስልጠና የተሰባሰቡ አፍለኛ ወጣቶች የጥበብ ጥሪያቸውን ጥማት ለማርካት ዘግይተውም ቢሆን ማኅበር መስርተዋል። በ1984 ዓ.ም ማኅበራቸው በከተማ አስተዳደሩ የባህል ቢሮ ፈቃድ አግኝቶ የክበቡ አባላትም በስነ ጽሁፍና በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች መሰባሰብ፣ መወያየት፣ መከራከር ቀጠሉ። መጀመሪያ ላይ 'የወጣት ደራሲያን ማኅበር' በሚል ራሳቸውን ሰይመው በኋላ ለአቅመ ደራሲያን እንዳልበቁ ሲረዱ 'ፍካት የሥነ ጽሁፍ ክበብ' በሚል ስማቸውን አሻሽለዋል። 'ፍካት' ቋሚ መሰብሰቢያ ሳይኖራት ከግለሰብ ቤት እስከ ህዝብ አዳራሾች በመዘዋወር በኪራይም በትብብርም የኪነ ጥበብ ድግስ እየደገሰች፣ በድግሱም አንጋፋ የስነ ጽሁፍ ሰዎች በእንግድነት እየጋበዘች ረጅም ርቀት ተጉዛለች። በ1987 ዓ.ም ደግሞ 'ቅኔ ጳጉሜ'ን የሚል የኪነ ጥበብ ዝግጅት በመጀመር እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ቀጥላለች። የ'ፍካት ሥነ ፅሁፍ ክበብ' ጉዞ ግን የአባላቱ የሕይወት መስመር በየፊናው ሲዘረጋ ሕልውናዋ መቋረጡ አልቀረም፤ ከ20 ዓመታት በኋላ ግን በትናንተናው ዕለት 'ዝክረ ቅኔ ጳጉሜ' በሚል መርሃ ግብር አባላቱ ዳግም ተገናኝተው ትዝታቸውን ተጨዋውተዋል። በ'ዝክረ ቅኔ ጳጉሜ' ዝግጅት በሊቀ ጉባኤያቱ የተመራ የአብነት ተማሪዎች ቅኔና የእስልምና ሊቃውንት ትንቢታዊ ግጥሞችን ያካተተ ዝግጅትን ጨምሮ የ'ፍካት' አበርክቶት ተወስቷል። በመድረኩ ከተወሱ የፍካት አበርክቶዎች መካከል ሌሎች የኪነ ጥበብ ክበባት ማጠናከሯ፣ ብርቱ የስነ ጽሁፍ ጥናቶችና ውይይቶችን ማካሄዷ፣ ዕውቅ የስነ ፅሁፍ ሰዎችን በመጋበዝ ከአባላቱ በተጨማሪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተሞክሮ የተሸጋገረባት፣ የሴት ገጣሚያን ማሰባሰብ፣ የሴት ደራሲያን ማኅበር እንዲቋቋም፣ የአባላቱ የሚዲያ ተሳትፎ እንዲፈጠር ማድረጓ ይገኙበታል። እንዲሁም 'ዜማ' በሚል መድብል ከ10 በላይ የፍካት አባላት የስነ ጽሁፎች የአጫጭር ልቦለድ ስራዎች ለሕትመት ብርሃን በቅተዋል። በአብዛኞቹ የራስ ቅል ላይ ነጭ ጸጉር የፈነጠቀባቸው የወቅቱ የፍካት መስራች አባላት ዛሬ ላይ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች፣ ደራሲያንና ከኪነ ጥበብ ሙያ ውጭም የተሰማሩ ሆነዋል። በወቅቱ በፍካት እንግድነት ከተጋበዙ ፍካት እንድትፈካ ከተመኙ የወቅቱ ደራሲያን መካከል ታደሰ ሊበን፣ ደበበ ሰይፉ፣ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር፣ አስፋው ዳምጤ፣ የሺጥላ ኮከብ፣ ሃይለመለኮት መዋዕል፣ አያልነህ ሙላቱ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ፈቃደ አዘዘ ይገኙበታል። በወቅቱ የ43 ዓመት ደራሲ የነበረው የዛሬው የ69 ዓመት አንጋፋ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፤ ፍካቶችን ከ20 ዓመታት በኋላ ሲያገኛቸው በአዕምሮም በእድሜም መብሰላቸውን ገልጿል። ሌላው በወቅቱ በፍካት ዝግጅቶች ከተጋበዙት ሌሎች የጥበብ ቤተሰቦች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋው የስነ ፅሁፍ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋውም ትውስታቸውን አጋርተዋል። ፍካት የአጭር ልቦለድ ደራሲው ታደለ ሊበን በሕይወት መኖሩን ያሳወቀችና በአካል ያገኙበት መድረክ መሆኗን፣ ለብዙ ደራሲያን መሰረት የጣለች፣ ለህትመት የበቁ አጫጭር ልቦለዶች ለማስተማሪያነት እየተጠቀሙባቸው እንዳሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ አንጋፋው ሰዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህም በ'ዝክረ ቅኔ ጳጉሜ' ታድመው ነበር፤ እርሳቸውም የፍካት ፍሬዎች ትልቅ የአገር ሃብት መሆናቸውን ተናግረዋል። ከፍካት አባላት መካከል አብዛኞቹ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩና የተለያዩ የድርሰት መጻሕፍትን ያበረከቱም ናቸው። ከነዚህም መካከል አለማዬሁ ገላጋይ፣ ዳንኤል ብርሃኑ፣ ብዙነህ ወልደዮሃንስ፣ በቀለ ሙለታ (አንቀጸ ደስታ)፣ ፍሬው አበበ፣ አለማየሁ ታዬ፣ እመቤት ዘውዴ፣ ጌታቸው ሰናይ፣ አሰፋ መኮንን፣ አስቴር በዳኔ፣ እንድሪያስ ተረፈ፣ ዮሴፍ ሃይለማርያም (ምርኩዝ ከጉለሌ) መጽሃፍት ካላቸው የፍካት አባላት መካከል ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ነብዩ ጥዑመልሳን፣ ጀማል አህመድ፣ ታደሰ ማሞ፣ ዮሴፍ ጌታቸው፣ እመቤት አብዲሳ፣ አይናለም ደፈረሱ፣ እያደር አዲስ ሌሎች በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሚገኙ ሲሆን ራሄል ተሾመና እልፍነሽ ሰይፉ በተውኔት፣ ዶክተር ተስፋዬ አበበ፣ አሰፋ መኮንን ሌሎች አባላት ደግሞ በተለያዩ የመንግስትና የግል ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል። ዛሬ ላይ ከ13 ያላነሱ መጻሕፍትን ያበረከተውና የፍካት ፍሬ የሆነው ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ደራሲ ቤት ዘግቶ ይጽፋል ቢባልም የፍካት ክበብ ለንባብም፣ ስህተትን ለማረም፣ የስነ ጽሁፍ አውድን ለመረዳት፣ ለሂስ በአጠቃላይ ለድርሰት ስራዎቹ መሰረት እንደጣለችለት ይናገራል። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ /ኢቢኤስ/ ስራ እስከያጅ የሆነው አቶ ነብዩ ጥዑመልሳን የወቅቱ የፍካት ሥነ ጽሁፍ ክበብ ሰብሳቢ የነበረ ሲሆን ፍካት በንባብ፣ በንግግር፣ በጽሁፍ እንዲበለጽግና በህይወት ጉዞው አብሮት የተጓዘ የጥበብ ስንቅ መሆኗን ያነሳል። ከፍካት ሌሎች አባላት መካከል አንዱ የሆነው አቶ ተስፋዬ ጸጋዬ በአሁኑ ወቅት በጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማራ ሲሆን የጥብቅና ሙያ የሚፈልገውን የመናገር፣ የመጻፍ፣ የማድመጥና የማንበብ ክህሎት እንዲኖረው ፍካት ውለታ መዋሏን፣ ዛሬም ድረስ የስነ ፅሁፍ ፍቅሩ እንዳልተለየውና የግጥም መድብል ማሳተሙን ያነሳል። ሶሰትም የፍካት አባላት ''በቀጣይ የቀድሞ ማኅበራቸውን ዳግም በማጠናከር ልምዳቸው ለወጣት ደራሲያን የሚያሸጋግሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር እናደርጋለን'' ብለዋል።