ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 ዘጠኝ ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞችና አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳሉ። ነገ ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ከፌደራል ማረሚያ፣ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከፌደራል ፖሊስ በተመሳሳይ ጠዋት 3 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ጠዋት 3 ሰዓት መከላከያ ከከምባታ ዱራሜ፣ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ላይ ደግሞ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ20 ነጥብ ሲመራ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና መቐለ ከተማ ተመሳሳይ 17 ነጥብ ይዘው በግብ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ቡታጅራ ከተማ 2 ነጥብ ብቻ በመያዝ የመጨረሻው ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የአራት ሳምንት የጨዋታ መርሃ ግብሮች የሚቀሩት ሲሆን  መርሃ ግብሩን ለማስተካከል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም