ኤጀንሲው 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ
መቀሌ (ኢዜአ) ጳጉሜን 3 ቀን 2011ዓ.ም --- የትግራይ ክልል ግብርና ምርቶችና ፕሮሞሽን ኤጀንሲ በተያዘው በጀት ዓመት 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ የግብርናና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ። ኤጀንሲው በ2011ዓ.ም የሥራ አፈፃፀምና በ2012 ዕቅድ ላይ በአዲግራት ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል። በውይይት መድረኩ ላይ የኤጀንሲውን ሪፖርት ያቀረቡት በተቋሙ የልማታዊ እቅድና የሰው ኃይል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍፁም ሀድጉ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የእንስሳት ተዋጽኦ እና የግብርና ውጤቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ተችሏል። ዘንድሮ ለውጭ ገበያ ከተላኩ 730ሺህ 595 ኩንታል ሰሊጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች 124 የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል። አቶ ፍጹም እንዳሉት በገበያው የሰሊጥ ምርቱን በብዛት ከተጠቀሙ ሀገሮች መካከልም ቻይና እና እስራኤል ቀዳሚዎቹ ናቸው። አቶ ፍጹም እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የተላከው ምርትና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በ20 ሺህ ኩንታል ምርትና በ4 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው። ብልጫ ያሳየበት ምክንያትም አርሶ አደሮችና በዘርፉ የተሰማሩ ሕብረት ሥራ ማህበራት ጥራትና ብዛት ያላቸው ምርቶች እንዲያቀርቡ የተሻለ ድጋፍና ክትትል መደረጉ መሆኑን ነው ያስረዱት። እንደ አቶ ፍጹም ገለጻ በ2012 በጀት ዓመትም ኤጀንሲው 150 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት የሚያስችሉ ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ግምት ያላቸው የሰሊጥ፣ የአትክልትና ፍሬፍሬ፣ የማርና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ እቅድ ተዘጋጅቷል። በውይይት መድረኩ ከተገኙ ባለድርሻ አካላት መካከልም የትግራይ ክልል ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸው"ጥራትና ብዛት ያላቸው ምርቶች ለማቅረብ የሚሰሩ ከ600 በላይ ሁለገብ ሕብረት ስራ ማህበራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንሰራለን" ብለዋል። አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶች እንዲያቀርብ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ክልል እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሚካኤለ ምሩፅ ናቸው ። በአዲግራት ከተማ በተዘጋጀው በእዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከ150 በላይ አመራሮች፣ የእርሻ ባለሙያዎችና የሕብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።