ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሃገራት የሚተርፍ መከላከያ ሠራዊት ገንብታለች

አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 5/2011 ኢትዮጵያ የውስጥ ሠላምን አስጠብቆ ለጎረቤት ሃገራት የሚተርፍ መከላከያ ሠራዊት ገንብታለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ እዝ በሀረር ከተማ አዲሱን ዓመት ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር አክብሯል፡፡ በመድረኩም ትናንት ከሰዓት የቀድሞና የአሁን ከፍተኛ የሰራዊቱ አዛዦች በተገኙበት የቀጠናው ሁኔታና የአገሪቷ የመከላከያ ሠራዊት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል፡፡ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦሩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ሰፊና አስቸጋሪ የቀጠናው ሁኔታ ውስጥ ያለች ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ቀጠና ውስጥ የሽብር እንቅስቃሴዎች የሀገራት የውስጥ ግጭቶች በሰፊው የሚስተዋሉበት መሆኑንም እንዲሁ ተናግረዋል፡፡ እንደዚህም ሆኖ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአገሩ አልፎ ለሌሎች ጎረቤት ሃገራት አለኝታ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ ሠራዊቱ በህገ መንግሥት የተገነባና ከሀገሪቷ ዜጎች በላይ ያልሆነ እንዲሁም ራሱን ለህዝብ አሳልፎ የሰጠ ሠራዊት ነውም ይላሉ፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ሀገሪቷ ውስጥ በቅርቡ የተፈጠሩትን ችግሮች በከፍተኛ ብቃትና ብስለት እየፈታ መገኘቱን ነው፡፡ ለአብነትም በሱማሌና በደቡብ ክልል በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በማረጋጋት ብቃቱን አስመስክሯል፡፡ በቀጣይም ሠራዊቱ የአምናው ዓይነት ግርግርና ሁከት እንዳይከሰት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ መንግሥትም የሠራዊቱን አኗኗርና ጥቅም ለማሻሻልና የተከበረ ሠራዊት ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባህር ኃይሉን የማጠናከር ሥራም በስፋት እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ኢታ ማዦር ሹሙ፤ የምድር ኃይል የማቋቋም ሥራም እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የቀድሞ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ተንሳይ ሠራዊቱ እስካሁን የገነባውን ስምና ዝና ይዞ እንዲቀጥል አመራሮቹ በየጊዜው ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል፡፡ ሠራዊቱ ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን የፖለቲካ ችግር ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመወጣት የሄደበት ርቀትም የሚደነቅ መሆኑን ጄኔራሉ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እንዲሁ ሠራዊቱ ጠንካራ ልምድና መልካም ሰብዕና የተላበሰ መሆኑን መመስከር ይቻላል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሠራዊቱ በዚሁ ሥነ ምግባር ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ሠራዊቱ በተለያዩ ጊዜያት ከሚሰነዘሩበት አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ራሱን ቆጥቦ የሀገሪቱን ሉአላዊነት እንዲያስጠብቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም