በመዲናዋ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግር እንደሆነባቸው ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግር እንደሆነባቸው ነዋሪዎች ገለጹ
ጳጉሜ 5/2011 በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ለቀናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየተቋረጠ መሆኑ ለአላስፈላጊ ወጪ ዳርጎናል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ። ቅሬታቸውን ለኢዜአ የገለፁት የከተማዋ ነዋሪዎች መፍትሄን ለማግኘት ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም ፈጥኖ ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም። የከተማዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ በበኩሉ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድ ትራንስፎርመር ከሚያቀርብ አዲስ ድርጅት ጋር ውል መፈራረሙን አስታውቋል። ነዋሪዎቹ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው አንድ ሳምንትና ከዚያ በላይ የሆኑ ቀኖችን እንዳሳለፉ ነው የተናገሩት። በዚህም እህል አብስለን የምንበላበት በመጥፋቱ ገንዘባችን ለብክነት ተዳርጓልና መንግስት ሊመለከተን ይገባል ይላሉ። አገልግሎቱ መቋረጡ የመኖሪያ አካባቢያቸው በጨለማ እንዲዋጥ በማድረግም ለዝርፊያ እንዳጋለጣቸው ጭምር ተናግረዋል። ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጊዜ ቢያመለክቱም "ምላሽ ሳናገኝ በርካታ ቀናትን በጨለማ እንድናሳልፍ ተገደናልም" ይላሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንደሀገር እየገጠመ ያለና ችግሩን ለመፍታትም እየተሰራበት መሆኑን ገልጿል። የዝናብ ወቅት ላይ መሆኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በንፋስና ዝናብ ለተደጋጋሚ ብልሽት እንዲጋለጥ አድርጎታል ያሉት የቢሮው ሪጅናል ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ ናቸው። ደንበኞች አገልግሎቱ ሲቋረጥባቸው 905 ነጻ የስልክ መስመር እየደወሉ ጥቆማ እያደረጉ አይደለም ያሉት አቶ በቀለ ጥቆማ ካደረጉም ዘግይተው በመሆኑ አፋጣኝ ጥገና ሳይደረግ ቀናት እንዲያልፍ ያደርጋል ብለዋል። ለኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የትራንስፎርመር ብልሽት መሆኑንም ተናግረዋል። ትራንስፎርመር የሚያመርተው ድርጅት በወቅቱ ትራንስፎርመሩን እያቀረበ አለመሆኑ የሚሰጠው ጥገና እንዲዘገይ እንዳደረገም ገልፀዋል። ችግሩን ለመፍታትም ከሌላ አምራች ድርጅት ጋር ውል ተፈራርመን በቅርብ ችግሩን እንፈታለን ብለዋል።