ቀጥታ፡

አልነጃሺ ሰው ልዩነት ሳያሳይ የኖረበት ታሪካዊ ስፍራና ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ነው...ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

መቀሌ ኢዜአ ጳጉሜን 4/ 2011-አልነጃሺ ሰው በሃይማኖቱ፣ በቋንቋውና በባህሉ ምንም ልዩነት ሳያሳይ በሰላምና በጋራ የኖረበት ታሪካዊ ስፍራና ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። 1ሺህ 441ኛ የአሹራ በዓል በአልነጃሺ መስጂድ በድምቀት ዛሬ ተከብሯል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት አልነጃሺ የውጭ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጰያውያንም ብዙ ሊያውቁት የሚገባ ታሪካዊ ስፍራ ነው። አልነጃሺ በቋንቋ፣ በባህልና በዕምነት የማይገናኙ ህዝቦች በጋራና በሰላም የኖሩበት ስፍራ መሆኑንም አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች በማንነታቸውና በቋንቋቸው ለጥቃት የሚጋለጡበት አጋጣሚ መስተዋሉን የጠቆሙት ዶክተር ደብረጽዮን “ከአልነጃሺ ስለሰላምና አብሮነት መማር ይቻላል” ብለዋል። አልነጃሺ ታሪካዊነቱ በዓለም አቀፍ ጭምር ጎልቶ እንዲታወቅ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ድጋፉን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው አልነጃሺ የመልካምነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣  የትግራይ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ መሆኑን አመልክተዋል። በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገኙ ምዕመናንን ጨምሮ ከሱዳን፣ ኤርትራና ከጅቡቲ የመጡ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም