የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራትን መገንባት ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራትን መገንባት ይገባል - ምሁራን
አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 4 / 2011 በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራትን መገንባት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ። ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት የትናንቱን ከመውቀስ ባለፈ ዛሬ ያለበት ሂደትም መገምገም ይኖርበታል ተብሏል። ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው የሚሰሩበት ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠር አለበትም ብለዋል። የዴሞክራሲን ቀን "በመደመር እሳቤ ጠንካራና ዘላቂ ዴሞክራሲን ለመገንባት እንነሳ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል። በመርሃ ግብሩ ላይ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሰለሞን ንጉሴ እንዳሉት፤ "ዴሞክራሲን ለመገንባት ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል"። ሁሉን አሳታፊነት የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሰለሞን፤ ለዚህ ደግሞ የህግ የበላይነት መስፈን ይኖርበታል ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በኢትዮጵያ "አንድ ትክክለኛ ጥያቄ አንድ ትክክለኛ መልስ" የሚል አካሄድ ዴሞክራሲውን እንዳቀጨጨው ገልጸዋል። በየትኛውም አቅጣጫ ይምጣ የብዙሃን ድምጽመደመጥና የአናሳ ብሄረሰቦች መብት መጠበቅ ይኖርበታልም ብለዋል። የቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረንስ ፎር ዴሞክራሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ በበኩላቸው ባለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ያገኘናቸውን መልካም አጋጣሚዎች ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል ብለዋል። በመሆኑም ካለፈው ስህተት በመማር የ 2010ሩን መልካም እድል በአግባቡ በመጠቀም ኅብረተሰቡ ዴሞክራሲን በተግባር እንዲኖረው ማድረግ ይገባናል ብለዋል። በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የትናንቱን መውቀስ ብቻ ሳይሆን የአሁንን አካሄድም መገምገም ይገባል ያሉት ደግሞ የመኢአድ ሊቀ መንበር አቶ ማሙሸት አማረ ናቸው። የኢህአፓ ሊቀ መንበር አቶ በላይነህ ንጋቱም ዴሞክራሲ በተግባር እንዲገለጥ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል። የታየውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ዘላቂ ለማድረግም በገዥው ፓርቲም ሆነ በሌሎች ተቋማት ላይ የህግ ጥሰት የሚፈጽሙ አካላትን መታገል ይገባናልም ብለዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ለመገንባት የዴሞክራሲን ጽንሰ ሃሳብ በተግባር መኖር ይገባልም ብለዋል ምሁራኑ። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በመሪዎች ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎም ጭምር የሚወሰን መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።