ሰላምን አስተማማኝ በማድረግ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን አስተማማኝ በማድረግ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል
ኢዜአ ጳጉሜ 4/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር ያለውን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ተናገሩ፡፡ የድሬዳዋ ልዩ መገለጫ የሆነውን የተጋመደ ህብረት በመንከባከብ የአካባቢያቸውን ሰላም እንደሚጠብቁ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ እንደተናገሩት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰላም ቀን መከበሩ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬዳዋ እየተመለሰ የሚገኘውን ሰላም በተቀናጀ መንገድ ለመጠበቅ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት በድሬዳዋ በተለያዩ አጋጣሚዎች የፀጥታና የሰላም መደፍረስ መከሰቱ የህብረተሰቡንየልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ነው ያስታወቁት፡፡ እንደ አቶ አህመድ ገለፃ የአስተዳደሩና የፀጥታ አካላት በየደረጃው ከሚገኘው ነዋሪ ጋር በመቀናጀት ባከናወኗቸው ተግባራት አሁን በድሬዳዋ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ''የተመለሰውን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ በማጠናከር የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ጠንክረን እየሰራን'' ብለዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብም ለዘመናት መገለጫ የሆነውን አንድነቱን በመጠበቅ የአካባቢውን ሰላምና ልማትበአስተማማኝ መንገድ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ወጣት ሰለሞን መክብብ በሰጠው አስተያየት በድሬዳዋ የተገኘውን ሰላም መጠበቅና ሀገር አቀፍ ለውጡን ዳር የማድረስ ትልቁ ኃላፊነት የወጣቱ ትውልድ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ''በተለያዩ አጋጣሚዎች ወጣቶችን ተገን በማድረግ ሰላም ለማደፍረስ የሚደረገው ጥረት የምንታወቅበትን ፍቅርና አንድነታችንን የማጠልሸት አላማ ያለው በመሆኑ በጥባጮችን በንቃት ለመከላከል ዝግጁ ነን''ብሏል፡፡ የኢጀ አነኒ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኡስማን አህመድ በበኩላቸው በገጠርና በከተማ የተጀመረው ልማት ውጤታማ የሚሆነው ሰላም በአስተማማኝ መንገድ በነዋሪው ሲጠበቅ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የድሬዳዋ የሀገር ሽማግሌ ሐጂ አብዱልወሃብ መሐመድ የሀገሪቱ ዜጎች መማር፣ መስራት፣ አግብተው ህይወትን መምራት የሚችሉት አስተማማኝ ሰላም በሀገር ሲረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰላም በጣም ውድ ሃብት ነው፤ ካመለጠ ዋጋ ያስከፍላል፤ በመሆኑም ወጣቱለሀገሩና ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በ2012 የትምህርት ዘመን 3 ሺህ 500 ተማሪዎች ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀው ለመማር ማስተማሩ ስራ መሳካት ሰላም መሠረታዊ ሃብት በመሆኑ ለሰላም ሁሉም ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስገንዝበዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበረው የሰላም መደፍረስ ዘንድሮ እንዳይደገም የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ''ከሰላም መጥፋት አንድም አካል አያተርፍም'' ያሉት ዶክተር ያሬድ''ተማሪዎች ለሰላም ትልቅ ዋጋ እንዲሰጡ ሰፊ የውይይት መድረክ ይካሄዳል'' ብለዋል፡፡