የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሚገባው በስንት ሰዓት ነው? - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሚገባው በስንት ሰዓት ነው?
አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 4 / 2011 በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ሲመጣ በተለይ መገናኛ ብዙሃን ከዋዜማው ጀምሮ ልዩ የበዓል ዝግጅት ለማቅረብ ዝግጅታቸውን የሚያጠናቅቁት አስቀድመው ነው። ተከታዮቻቸውን ያዝናናሉ ያሳውቃሉ፣ ያስተምራሉ ያሏቸውን ከተለያዩ ቦታዎች የበዓል ፕሮግራሞች ያስተላልፋሉ። በተለይ በዋዜማ ምሽት በተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎችና በመገናኛ ብዙሃን ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ርችቶች ይተኮሳሉ፤ የመልካም ምቾት መግለጫዎች ይተላለፋሉ። ለመሆኑ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሚገባው ስንት ሰዓት ነው? ሲል ኢዜአ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል። ከአብዛኛዎቹ መላሾች ያገኘነው መልስም የጳጉሜ መጨረሻ ቀን ከለሊቱ ስድስት ሰዓት የሚል ሆኗል። ይህ ሰዓት ለምን የአዲስ ዓመት መግቢያ ብስራት እንደሆነ ግን ትክክለኛ መረጃ እንደሌላቸው ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ግን መገናኛ ብዙሃኑም ሆኑ ሌሎች አካላት በየዓመቱ ከለሊቱ ስድስት ሰዓት የሚያውጁት የአዲስ ዓመት ብስራት "ትክክል አይደለም" ይላሉ። የዘመን መለወጫ የሚገባበት ሰዓት ወጥ አለመሆኑንና ከዓመት ዓመት ሰዓቱ የሚቀያየር መሆኑንም ያወሳሉ። በመሆኑም የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በአራቱም ዓመት የዘመን መለወጫ ሰዓት በተለያየ ሰዓት የሚገባ መሆኑን ነው ያብራሩት። ይህ የዘመንና የሰዓት አቆጣጠር በቤተክርስቲያኗ በተደራጀ መልኩ ተተንትኖ በመጽሐፍ መኖሩንም ገልጸዋል። ይህን የኢትዮጵያ ሃብት ብቻ የሆነውን የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያኑ ጋር በማመሳሰል በዘፈቀደ ሰዓቱን ማወጅ ተገቢ አለመሆኑንም ነው የገለጹት። አዲሱን ዓመት ያስረጀነውን አስተሳሰብ ጥለን ከተፈጥሮ እኩል ራሳችንን አዲስ የምናደርግበት፤ ይቅርታና ምህረት ባህል የሚሆንበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ከዚህ ጋር በተያያዘ በ2002 ዓ.ም በዚሁ ጉዳይ አንድ ጽሁፍ ጽፏል። በጽሁፉም ''ፈረንጆቹ በእኩለ ሌሊት አዲስ ዓመታቸውን ቢቀበሉ እውነታቸውን ነው፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ የቀን አቆጣጠር ከእኩለ ሌሊት አንድ ሰዓት አልፎ ይጀምርና በእኩለ ሌሊት ያልቃል፡፡ አዲሱ ዓመታቸውም 00 ብሎ የሚጀምረው በእኩለ ሌሊት ነው፡፡ ኮፒ በሚጠቅም መንገድ ከተደረገ አንዳንድ ጊዜ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ኮፒ ሲደረግ ለገልባጩ እንዲያመቸው አድርጎ ካልሆነ ከመኮረጅ የባሰ ስሕተት ይሠራል።''ነው ያለው። ''ፈረንጆቹ አዲሱን ዘመናቸውን የሚቀይሩት በእኩለ ሌሊት ነው፡፡ያም እንኳ ቢሆን ትክክል ሆኖ አይደለም፡፡ የዘመን መለወጫ በሽርፍራፊ ሴኮንዶቹ የተነሣ በየጊዜው ይለዋወጣልና፡፡ ነገር ግን በልማድ ሕግ /customary law/ መሠረት በእኩለ ሌሊት ሰዓታቸውን በመጀመራቸው ከሰዓታቸው ጋር እንዲገጥም አድርገው ተጠቀሙበትና በዚያው ጸና፡፡ ታድያ እኛም ለመሠልጠን እንደ እነርሱ በእኩለ ሌሊት አዲሱን ዓመት መቀበል አለብን ተብሎ ሳይታሰብ አልቀረም፡፡''ነው ያለው።