የዋጋ ንረትን ለማስተካከል የሚያስችል እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ንረትን ለማስተካከል የሚያስችል እርምጃ ተወሰደ
ጅማ ኢዜአ ጳጉሜን 4/ 2011፣ በጅማ ከተማ በሽንኩርት ዋጋ ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል የሚያስችል እርምጃ መውሰዱን የጅማ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጅማ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ሽፈራው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በከተማው ባለፈው ወር የአንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ዋጋ 50 ብር ደርሶ ነበር፡፡ በተሰራው የቁጥጥር ስራም ዋጋውን ከ18 ብር እስከ 30 ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ የዋጋ ንረት ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ሁለት ጅምላ የሽንኩርት ነጋዴዎች መጋዘናቸውን የማሽግ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ሌሎች ሁለት ነጋዴዎች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ በከተማው ቢሺሼ በሚባለው ትልቅ የገበያ ስፋራ ላይ የችርቻሮ ፈቃድ አውጥተው የጅምላ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት በዋነኝነት የዋጋ ንረት እየፈጠሩ እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ''እራሳቸው ሲቸረችሩ በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡ ሲሆን ጅምላ ሲያከፋፈሉ ግን በውድ ዋጋ በመሽጥ የዋጋ ንረት በመፍጠር ህብረተሰቡን እየጐዱ ይገኛሉ'' ብለዋል፡፡ ''ይህንን ችግር ለመፍታትም በጊንጆ ጉድሩ ቀበሌ አዲስ የገበያ ስፍራ በማዘጋጀት 32 የሽንኩርትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ስራ እንዲጀምሩ ተድረጓል'' ብለዋል፡፡ ይህም ጅምላና የችርቻሮ ነጋዴዎችን ለመለየት ከማስቻሉም በላይ የቢሺሼ ገበያ ያለበትን የገበያ መጨናነቅ እንደሚያቃልል ተናግረዋል፡፡ በቢሺሼ ገበያ የሽንኩርት ነጋዴ የሆኑት አቶ ሽኩር ሱልጣን እንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ጅምላ ነጋዴዎች ከችርቻሮ መለየቱ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ ከቢሺሼ ገበያ ሸማች የሆኑት ወይዘሮ አይናለም ተስፋዬ በበኩላቸው ከሳምንት በፊት የነበረው የሽኩርትና የፍራፍሬ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በዚህ ሳምንት መቀነስ በማሳየቱ ተደስቻለሁ ያሉት አስተያየት ሰጪዋ ለአመት በዓል የሚያሰፈልጋቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመግዛት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው አካል ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ የሚያደረጉ አካላትን ለመቆጣጠር የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡