ህዝቡ ለሰራዊቱ የጀግንነቱ ኃይል ነው--- ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ ለሰራዊቱ የጀግንነቱ ኃይል ነው--- ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ
ሀረር ጳጉሜ 4/ 2011 "ህዝቡ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የግንነቱ ኃይል ነው " ሲሉ በሀገር መከለከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ ገለጹ። በዕዙ አዘጋጅነት በሐረር ከተማ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ሜጀር ጀነራሉ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በከተማው በተለያዩ ስፍራዎች ትናንት የፅዳት ስራ አከናውነዋል፡፡ በዚህ ወቅት ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ እንዳሉት በመከላከያ ደረጃ በሀረር ከተማ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ዕዙ ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ "ከህብተረተሰቡ ጋር በመተባበር እያከናወንናቸው ካሉ ተግባራትም የፅዳት ዘመቻው አንዱ ነው" ብለዋል፡፡ ዕዙና ሀረር ከተማ የረጅም ጊዜ ትስስር እንዳላቸው የጠቆሙት አዛዡ በዓሉ ይህንን ግንኙነት ለማጎልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ "ህዝቡ ለሰራዊቱ ጀግንነት ኃይል ነው " ያሉት አዛዡ ሰራዊቱም ህዝቡም ይህንን እንደመገነዘብ ገልጸዋል። በተለይ በመከላከያ ደረጃ ዛሬ በሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል ላይ በንቃት በመሳተፍ እንደሁልጊዜው የሰራዊቱ ደጋፊ መሆኑን እንዲያሳይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በጽዳት ስራው ከተሳተፉት የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ቤዛ መሻሻ "ከማለዳ ጀምሮ በጽዳት ዘመቻው በመሳተፍ የመከላከያ ሰራዊቱ አጋር መሆናችንን እያሳየን እንገኛለን" ብላለች፡፡ እንደ ወጣት ቤዛ ገለፃ ቆሻሻ ከአካባቢያ ቸው እንዳጸዱ ሁሉ ጥላቻንና ቂምን ከውስጣቸው ማስወገድይገባል፡፡ ኢሊያስ ሁሴን የተባለ ሌላው ወጣት በበኩሉ " በፅዳት ዘመቻው በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ በቀጣይም ለሚያስፈልጉ ትብብሮች ተሳትፎዬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብሏል፡፡ በመከላከያ ሰራዊቱ እና በነዋሪው መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቁሞ ከወራቶች በፊት በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግርን ከመፍታት አንፃር ሰራዊቱ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውሷል፡፡ " ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በአንድነት የፅዳት ዘመቻ አከናውነናል " ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አረፋት አብዱረሃማን ናቸው። ይህም የማይጠቅም አስተሳሰብ ከውስጥ በማስወገድ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።