ቀጥታ፡

በክልሉ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ እየተሰራ ነው----የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ነሀሴ 30 ቀን 2011  በክልሉ ያለበቂ ምክንያት በተለያዩ ምርቶች ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡ የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወጤ ቶሼ እንደገለጹት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ጤናማ የንግድ ሥርዐት እንዳይፈጠር አድርገዋል። በሀገር ደረጃ የተስተዋለው የአቅርቦት እጥረት እንዲሁም በክልል ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የግብርና ምርት መቀነሱ የምርቶች ዋጋ በተወሰነ ደረጃ እንዲጨመር ማድረጉን አመልክተዋል ፡፡ እንደ አቶ ወጤ ገለጻ በክልሉ በአጠቃላይ ዘንድሮ ለገበያ የቀረበው የግብርና ምርት አምና ከነበረው በ10 ሚሊዮን ኩንታል ቀንሷል፡፡ በዚህም ምክንያት በብዕርና አገዳ ሰብሎች፣ አትክልትን ፍራፍሬዎች፣ ጥራጥሬና ቅመማቅመሞች እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ አቶ ወጤ እንዳሉት አንዳንድ ራስ ወዳድ ነጋዴዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ምርቶችን ያለ አግባብ አከማችተው እጥረቱ እንዲባባስ በማድረግ የምርቶች ዋጋ ያለአግባብ እንዲባባስ አድርገዋል። በመንግስት ድጎማ ለሕብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ለገበያ እንዲውል በማድረግ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጫና ያሳደሩ ግለሰቦችም መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ቢሮውና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቁጥጥር መላላት ለዋጋ ንረት የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት። የግንባታ ዕቃዎች ፋብሪካዎች ዋጋ ሳይጨምሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ሀገራዊ ሁኔታውን በማየት ዋጋ እንዲባባስ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። እንደዳይሬክተሩ ገለጻ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት አቅም ማነስና በጥቂት ምርቶች ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢሮው ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ግበረ-ኃይል አቋቁሞ በተጠናከረ መልኩ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ወጤ፣ የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰድ እንደጀመሩም ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የሰብል ምርቶችን ያለ አግባብ የሚያከማቹ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር መጋዘኖችን የመፈተሽ ሥራ መጀመራቸውን ነው የገለጹት፡፡ በድጎማ የሚቀርበው ስንዴ በሕገ-ወጥ መንገድ ለገበያ የሚያውሉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን በእዚህም በርካታ አቅራቢ ነጋዴዎችና ዳቦ ቤቶች ከአቅርቦት ትስስሩ እንዲወጡ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት እንዲሁም ከነጋዴዎች ጋር በመተባበር ምርት ካለበት አካባቢ ፍላጎት ወደጨመረበት አካባቢ እንዲመጣ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ግልጸዋል፡፡ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት አቅማቸውን አጎልብተው የእለት ተዕለት የፍጆታ እቃዎችን ለተጠቃሚዎች በተሻለ ማቅረ እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ያልተገባ የንግድ አሰራር ሲገጥመው በ8034 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል መጠቆም እንደሚችል አስታውቀዋል። እንደ አቶ ወጤ ገለፃ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ለሁለት ወራት በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው የዘይት፣ የስኳር ናየዳቦ ዱቄት አቅርቦት በአሁኑ ወቅት ችግሩ በመፈታቱ ከበዓል በፊት ለተጠቃሚዎች የማድረስ ስራ እየተሰራ ነው ፡፡ በእህል ንግድ ሥራ ተሰማሩት አቶ ለማ አሸናፊ በበኩላቸው ጭማሪው ከወራት በፊት እንደሆነ ገልጸው በተለይ ጤፍና በቆሎ ከሩቅ መምጣቱ የትራንስፖርት ወጪውን እንደጨመረባቸው ገልጸዋል። "የግብር ምርቶች በእህል አቅራቢ ማህበራት አማካኝነት ለነጋዴው እንዲቀርቡ ቢደርግ ለሸማቹም በተሸለ ዋጋ ማቅረብ ይቻላል" ሲሉም ጠቁመዋል ፡፡ እህል ሲገበያዩ የነበሩት የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ታደለች ዲደራሻ በበኩላቸው አንደኛ ደረጃ ጤፍ በኩንታል እስከ 3 ሺህ 400 ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ገልፀው ካለፉት ወራት ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋው እየጨመረባቸው መምጣቱን ተናግረዋል ፡፡ በርበሬ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች ምርቶችም እንደዚሁ ዋጋቸው እየናረ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ታደለች መንግስት ገበያውን እንዲያረጋጋላቸው ጠይቀዋል ፡፡ አቶ ሚልኪያስ ሎምቤዎ የተባሉ ዋሪ በበኩላቸው ቆርቆሮ፣ ምስማርና ሌሎች የግንባታ እቃዎችን መሸመታቸውን ገልፀው አንዳንድ ነጋዴዎች ምርቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ የሚሸጡበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል። ሕብረተሰቡ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለሚመለከተው አካል አሳልፎ መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም