ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ስኬታማ ነበር - አምባሳደሮች

አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 4 / 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ሰሞኑን በተለያዩ ሶስት አገራት ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ ነበር ሲሉ በኢትዮጵያ የአገራቱ አምባሳደሮች ገለጹ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት የልኡካን ቡድን ሰሞኑን በደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና እስራኤል ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጓል። ንግድና ኢንቨስትመንትን ማጠናከርን ጨምሮ በሌሎች የጋራ ዘርፎች ላይ ያተኮረውን ጉብኝት ተከትሎም የተለያዩ የትብብር ስምምነቶች ከየአገራቱ መንግስታት ጋር ተፈርሟል። አምባሳደሮቹ እንደተናገሩትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር የነበራትን የትብብር ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያገዘና በሌሎች መስኮች ላይም በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሰረት የጣለ ነበር ብለዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሊም ሆንሚን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪያ ጉብኝት የአገራቱን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ትልቅ እምርታ አለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳምሰንግን፣ ሃዩንዳይንና የደቡብ ኮሪያ የወጪና ገቢ ባንክን ከመሳሰሉ የደቡብ ኮሪያ ታላላቅ ኩባንያዎች  ጋር በትብብር መስራት በሚቻልበት መንገድ መምከራቸውን ገልጸዋል። ይህም ኩባንያዎቹ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተዋወቁ አድርጓቸዋል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ኮሪያ ቆይታቸው አምስት ስምምነቶችን የተፈራረሙ ሲሆን ከዚህ መካከልም ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የተደረገው የ86 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ጉብኝቱ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና በተለይም ደግሞ በአየር ንብረት ጥበቃ፣ በንግድ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልውውጥ መስኮች ትብብሩ እንዲስፋፋ አስችሏል ሲሉም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል። በአፍሪካ ኅብረት የጃፓን አምባሳደር ፉሚዮ ሺሚዙ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ለሰባተኛው የቶክዮ የአፍሪካ ልማት ስብሰባ (ቲካድ)ና ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ በጣም ወሳኝ ነበር ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለው የልማት ጉዳይም ሌላኛው የውይይት አጀንዳ ነበር  ያሉት አምባሳደር ሺሚዙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ የሚያደርጉትን ጥረትም ጃፓን የምትደግፍ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማትንና የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጃፓን ትደግፋለች ብለዋል። በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ደግሞ  የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስራኤል ጉብኝት የአገራቱን የረጅም ዓመት ታሪካዊ ግንኙነት ያጠናክራል። ጉብኝቱ በአገራቱ መካካል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር ሌሎች አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለማፈላለግና ለማሳደግ ያለመ እንደነበር አንስተዋል። በዋነኛነት በምጣኔ ኃብት በተለይም በግብርና  መስኖ ልማት እስራኤል ያላትን ትልቅ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል አገራቱ የሚሰሩ መሆኑም ተመልክቷል። እስራኤልና ኢትዮጵያ የሳይበርና የሽብርተኝነት ጥቃት ስጋት አለባቸው ያሉት አምባሳደሩ ከግብርና በዘለለ በሌሎች ዘርፎች ላይም ትብብር ለመፈጠር ተወያይተዋል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ነበር ጉብኝታቸውን በሶስቱም አገራት አጠናቀው ወደ አገራቸው የተመለሱት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም