ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መልካም ዕድሎች ቢኖሩም ፈተናዎችም የተጋረጡበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መልካም ዕድሎች ቢኖሩም ፈተናዎችም የተጋረጡበት ነው
አዲስ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 4 /2011 በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መልካም ዕድሎች ቢኖሩም የቆዩና አዲስ የተፈጠሩ ፈተናዎችም የተጋረጡበት እንደሆነ ተገለጸ። ጳጉሜን 4 ቀን "በመደመር እሳቤ ጠንካራና ዘላቂ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንነሳ" በሚል መሪ ሃሳብ የዴሞክራሲ ቀን ተብሎ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በሸራተን አዲስ እየተከበረ ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሰለሞን ንጉሴ፣ ደራሲና ተመራማሪ ወጣት መሐመድ አሊ (ቡርሃን) እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ዕለቱን አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት የመነሻ ሀሳብ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በኢትዮጵያ ሲወጡ የነበሩ ህጎችና የአሰራር ስርዓቶች ዴሞክራሲ እንዳያድግና እንዳይጎለብት ማድረጉን ገልጻለች። የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሸራረፍ በዴሞክራሲው ላይ ገደብ እንዲኖርና እንዳያድግ ችግር መፍጠሩንም እንዲሁ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የታዩ ችግሮች ለዚህ ማሳያ እንደሆኑና ይህም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ላይ ጥያቄ ማስነሳቱን ተናግራለች። አርሶ አደሩ፣ ሴቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች የመመለስና በጥልቀት የማየት ሁኔታ እንዳልነበረም አንስታለች። ያም ሆኖ አሁንም የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት መልካም ዕድሎችና አጋጣሚዎች መኖራቸውን ነው ሶሊያና ሽመልስ በመነሻ ጽሁፏ ያቀረበቸው። በመንግስት በኩል እየተደረጉ ያሉ የህግ ለውጦች፣ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት እየተሰሩ ያሉ የማሻሻያ ስራዎች እና በመንግስት በኩል ዴሞክራሲ ለማጎልበት የተሻለ ቁርጠኝነት መኖሩ እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚታይ ገልጻለች። ሆኖም ከህብረተሰቡ ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት አቅም ይህን ፍላጎትና ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን ነገር ለማሟላት ያላቸው ዝግጁነት ገና መሆኑ 'እንደ አዲስ ፈተና የሚታይ ነው' ብላለች። ተቋማቱ እየተደረገላቸው ያለው ማሻሻያ መልካም የሚባል ቢሆንም ከሚጠበቅባቸው ሃላፊነትና የቀደሙትን አሰራሮች ከመቀየር አንጻር ገና ብዙ ጊዜ እንደሚወስድም ጠቁማለች። ተቋማቱ የነበሩበት አደረጃጀትና ሲከተሉት የቆዩት አሰራር ያዳከማቸው በመሆኑ ሃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል ነው ያለችው። ጠንካራ ተቋማት ከመገንባትና የማሻሻያ ስራዎችን ከመከወን ባለፈ ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እንዲሳተፍ የማበረታታት ስራ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት አለማግኘቱና የዜጎችን ተሳትፎ ማሳደግ አለመቻሉ እንደ ተግዳሮት የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው ስትልም አብራርታለች። ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ማለት ህዝቡ በምርጫ ቀን ተሰልፎ በሰላማዊ መንገድ ድምፅ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ለምርጫው የተፈጠሩ መዳላድሎችና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊኖርበት የሚገባ በመሆኑ ከዚህ አንጻር ምርጫ ቦርድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አውስታለች። ደራሲና ተመራማሪ ወጣት መሐመድ አሊ (ቡርሃን) በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ መንገድ ያሉ አካላት የዴሞክራሲን መርህና ስነ ምግባር ተከትለው ከመጓዝ ይልቅ እርስ በእርስ የመደነቃቀፍ ችግር በስፋት የሚታይና የቆየ ችግር እንደሆነ ገልጿል። የመደነቃቀፉ ችግር የሚመነጨው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳቦች ብቻ ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደማይችሉና ጽንሰ ሀሳቦቹን በኢትዮጵያ ካለው እምነት፣ ባህልና አመለካከት ጋር ማዛመድ ባለመቻሉ ነው ብሏል። በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ ከሆኑት መካከል ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ የሀሳብ ክርክርን ከጎሰኝነት አስተሳሰብ የማቀላቀል ችግር ክርክሮችና የሀሳብ ፍጭቶች ጎሳዊ ጠባይ እንዲኖራቸው ማድረጉን ጠቅሷል። ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ እንደ ማህበረሰቡ ሁኔታ የሚለያይ መሆኑንና ኢትዮጵያን እንደ አንድ የሚገልጽ ትርጓሜ አለመቀመጡ ዴሞክራሲን በትልቅ ምስል ውስጥ እንዳይታይ ማድረጉንም አንስቷል። ለዴሞክራሲ ስርዓቱ ግንባታ መጎልበት የኪነ ጥበብ ዘርፉ፣ የትምህርት ተቋማትና የሃይማኖት ምሁራን ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ነው ደራሲና ተመራማሪው ወጣት መሐመድ አሊ (ቡርሃን) የገለጸው። በመንግስት በኩል የዴሞክራሲ ስርዓት ለማስፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መልካም ጅምር የሚባሉ እንደሆኑ የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግና አስተዳደር የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሰለሞን ንጉሴ ናቸው። ህብረ ብሔረዊነትና ጎሰኝነት እንዲሁም ብሔርን አስመልክቶ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶች ለዴሞክራሲ ስርዓት ፈተና እንደሆኑና በትኩረት ሊታዩ የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። የመናገርና የመጻፍ መብት የሌሎች ቡድኖችን መብት ሲገድብ፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልተቻለና የፖለቲካ ተዋናዮች ዴሞክራሲን ለመተግበር መንገራገጭ ከታየባቸው የዴሞክራሲ ሰርዓት ግንባታ ለፈተና እንደሚዳረግ አመልክተዋል። እኩልነት ሠላምና መረጋጋት፤ ጸጥታ ሰብአዊነትና ብልጽግና ያለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ 'ሊታሰቡ አይችሉም' ብለዋል። የህዝብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት፣ የህግ የበላይነት ማስፈን፣ የፖለቲካ ብዝሃነትን ማስፋት፣ በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲኖር ማድረግ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቁመዋል። ዴሞክራሲን 'የዴሞክራሲ ቀን' ብሎ በመዘከር ብቻ ማምጣት እንደማይቻልና ዴሞክራሲ የሚሰራ፣ የሚሻሻል፣ ሁልጊዜ ለውጥ የሚያስፈልገውና ስርዓቱን ለመገንባትም ጊዜ የሚወሰድና ትዕግስትን የሚጠይቅ እንደሆነም አስረድተዋል። ዴሞክራሲን መገንባት የጥቂት ግለሰቦች ስራ ሳይሆን 'የዜጎችን ቁርጠኝነትና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው' ብለዋል ዶክተር ሰለሞን። ይህ ዜና በተጠናቀረበት ሠዓት በቀረቡት መነሻ ጽሁፎች ላይ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠባቸው ይገኛል።