በሸማች ማህበራት የሚቀርቡ ምርቶች ከህብረተሰቡ ይልቅ ነጋዴውን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2011 በአዲስ አበባ በሚገኙ ሸማች ማህበራት የሚቀርቡ ምርቶች ከህብረተሰቡ ይልቅ ነጋዴውን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሆነ ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ሸማች ማህበር ለበአል የሚሆኑ ሸቀጦችን ስገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፍፁም በየነ እንዳሉት፤ የበአል ገበያን ለማረጋጋት ሽንኩርት፣ ቅቤ፣ እንቁላል፣ ዘይት፣ ዱቄትና ሌሎችም ምርቶች በብዛት ገብቷል ፡፡

በሸማች ማህበሩ የሸቀጦች ዋጋ ከውጭ ገበያ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ በጣም ትንሽ ቢሆንም ጥራቱን የጠበቀ በመሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው የተናገሩት ወይዘሮ ፍፁም፤  ከሱቅ  በምገዙበት ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን የሚዛንና መሰል ማጭበርበር  ታድጎናል ይላሉ።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው የአካባቢው ተጠቃሚዎች ፓልም ዘይት ለመከፋፈል ወቅቱ ክረምት ከመሆኑና ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ሲቸገሩ ሸማች ማህበሩ ለነጋዴ እንደሚሸጥ የተናገሩት  ወይዘሮ ፍፁም፤ ከተጠቃሚው ይልቅ ለነጋዴው ቅድሚያ የመስጠት አዝማሚያ  ይታያል ብለዋል።

በዚሁ ክፍለ ከተማ የሸማች ማህበሩ የረጅም ጊዜ ተገልጋይ  መሆናቸውን  የተናገሩት  አቶ ተስፋዬ  ከበደ፤ የበአል ገበያው ብቻ ሳይሆን የኑሮ ውድነቱ አሳሳቢ እየሆነ  መምጣቱን ይገልፃሉ፡፡

በውጭ ገበያ 4 ብር ከ50 ሳንቲም የሚሸጥ እንቁላል በ4 ብር፣ ሽንኩርት በኪሎ 27 ብር፣ በውጭ ገበያ አንድ ኪሎ ከ230-250 ብር የሚሸጥ ቅቤን በ180 ብር መግዛታቸውንም ተናግረዋል።

በማህበሩ የሚመጡ ምርቶች ከተጠቃሚው ይልቅ ነጋዴውን ተጠቃሚ እያሰደረገ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በአገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚስተዋለው የስነ ምግባር ችግርና ብልሹ አሰራር የህብረት ስራ ማህበሩ አመራሮች ሊፈትሹ ይገባል ብለዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ሸማች ህብረት ሥራ ማህበር ለበአል ፍጆታ የሚውሉ እንደ  እንቁላል፣ ቅቤ፣ ሽንኩርትና ዘይት ምርቶች  እንዳልገባ  የተናገሩት ወይዘሮ ፍፁም ታደለ     ህብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ሳይዳረግ ለበአል ፍጆታ የሚውሉትም ሆነ ሌሎች የጥራጥሬ እህሎች እንድቀርብላቸው ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ፤ በበአል ሰሞን ሊያጋጥሙ የሚችሉ እጥረቶችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል፡፡

የክፍለ ከተሞች ፅህፈት ቤት ሃላፊዎች፣ የግብይት ስራ ሂደት መሪዎች፣ ከቦርድ አመራሮችና ከዩኔኖች ጋር በመወያየት መግባባት ላይ ተደርሶ በእቅዱ መሰረት እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

እጥረት ያጋጥማል ተብለው ከተለዩት ምርቶች መካከል የጤፍ፣ምስር፣ሽንኩርት፣ ቅቤ፣ ዶሮ፣ የስጋ ከብት እና የመሳሰሉት ምርቶች ከአጎራባች ክልሎች ከሚገኙ አምራች ዩኒየኖች የምርት ትስስር ሰነድ ውል በመፈራረም ምርቶች መግባቱንም ገልፀዋል፡፡

በአልን ታሳቢ በማድረግ ከውጭና አገር ውስጥ አምራቾች ጋር በመነጋገር 496 ሺህ ሌትር በላይ የፓልም ዘይት፣ 296 ሺ እንቁላል፣ 3ሺህ 766 ኪሎ ግራም ቅቤ መግባቱንና ተጨማሪም እንደሚገባ አስረድተዋል።

በባለ 20 ሌትር ዘይት ለ4 እና ለ5 ሰዎች እንዲካፈሉ መደረጉ ከአመቺነትና አቅም አንፃር በህብረተሰቡ እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎችን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሰራተኞች በኩል የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርና የስነ ምግባር ብልሹነትን ለማረም ከሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመቀናጀት ከዲስፕሊን ቅጣት እስከ ማባረር ድረስ እርምጃ መወሰዱና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም