ቀጥታ፡

ኮሌጁ የመምህራን እጥረትን ለመቅረፍ እየሰራ ነው

ዲላ ኢዜአ ጳጉሜ 4/2011  የዲላ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በቅድመ መደበኛ የሚስተዋለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኮሌጁ በክረምትና በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 6 ሺህ 449 መምህራን ዛሬ በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡ በምርቃቱ ወቅት የኮሌጁ ዲን አቶ እርቅይሁን ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት በ20 የተለያዩ የትምህርት አይነቶች 6 ሺህ 449 ተማሪዎች በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ተመራቂዎቹ ላለፉት አራት አመታት ትምህርታቸውን በንድፈ ሃሳብና በተግባር ተከታትለው ያጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮሌጁ በመጀመሪያ የትምህርት ደረጃዎች ላይ በተለይም በቅድመ መደበኛ የሚስተዋሉ የመምህራን እጥረትን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል  200 የሚሆኑት በቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የሰለጠኑ መምህራን መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ማትዮስ ማንዳዬ በበኩላቸው በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ደረጃዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ተመራቂዎቹ የተጣለባቸውን ትውልድን በእውቀትና በስነ ምግባር የመቅረጽ ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው የተጣለባቸውን ትውልድ የማፍራት ከባድ ሃላፊነት በትጋት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡ ተመራቂዎች  መካከል መምህርት ትግስት ሀይቆ በሰጠችው አስተያየት ከስራ ገበታዋ ሳትነጠል በክረምት ወራት የትምህርት ደረጃዋን በማሻሻሏ እርካታ ተሰምቷታል ። በትምህርት ቆይታዬ ያገኘችሁን እወቅትና ክህሎት በመጠቀም ትውልድን የመቅረጽ ሃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ብላለች ። መምህር ዘላለም ተሰማ በበኩላቸው በኮሌጅ ቆይታቸው ከዚህ በፊት በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ያጋጥሙ የነበሩት ችግሮችን ለመቅረፍ  የሚያስችላው እውቀት መቅሰማቸውን ገልፀዋል ። በሚሰሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ በዜሮ ክፍል ያለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ የበኩሉላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም