የካቲት 12 ትምህርት ቤት የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ለመሆን ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካቲት 12 ትምህርት ቤት የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ለመሆን ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው

ጳግሜ 4/2011 የካቲት 12 (እቴጌ መነን) ትምህርት ቤት የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ :: ለተማሪዎች ለመቀበልም የማደሪያ፣ የመመገቢያ አዳራሽና የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ 80 በመቶ መከናወኑን ተገልጿል። አዳሪ ትምህርት ቤቶች በአፍሪካ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ይነገራል። ምንም እንኳን ሌሎች የአለም አገራት አዳሪ ትምህርት ቤት ባይኖራቸውም ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት ልዩ ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋሉ። አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይናና የመሳሰሉት አገራት ደግሞ ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በመደገፍ በምሳሌነትየሚጠቀሱ አገራት ናቸው። በኢትዮያ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ታሪክ ልክ እንደ እቴጌ መነን፣ ተግባረእድ፣ ወይዘሮ ስህንና ጄኔራል ዊንጌት ያሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የአገራችን ልዩ አዳሪ ትምህርትቤት ታሪክ ሲነሳ አብረው የሚነሱ ናቸው። የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ብሎም በሌሎች እንቅስቃሴዎች አገራትን በፊት አውራሪነት የሚመሩና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን የሚያፈሩ ናቸው። የካቲት 12(እቴጌ መነን) ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ እድሜ ጠገብ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ነው። ትምህርት ቤቱ በ1924 ዓ.ም ሥራ የጀመረ ሲሆን ሴቶችን ለማስተማር ዓላማ አድርጐ የተነሳ እንደነበርም ይነገራል። ይህም ከ1924 ዓ.ም እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ ብቸኛው የሴት ተማሪዎች ትምህርት ቤት በመሆን አገልግሏል። ከ1972 ዓ.ም እስከ 1993 ዓ.ም የሴት ተማሪዎች ብቻ መሆኑ ቀርቶ ሁሉንም ተቀብሎ የሚያስተናግድ ትምህርት ቤት በመሆንም ትምህርት ሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቱን ወደ ቀድሞ ማንነቱ ለመመለስ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት እንድሆን ለማድረግ እንስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መስተዳድር አቶ መሀመድ ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ 500 ሴት ተማሪዎችን ያስተናግዳል። ይህንንም በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለመጀመር በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙና ለረዥም አመታት እድሳት ሳይደረግላቸው የቆዩትን ህንጻዎች ቅርስነታቸውን ሳይለቁ የማደስና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። አዳዲስ የተማሪዎች ማደሪያ (ዶርም) እና የመመገቢያ አዳራሽ ግንባታዎችም 80 በመቶ መከናወኑን ተናግረዋል። የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በተለይም የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግቡ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሻለ ትምህርት ለማቅረብ እድል ይፈጥራል ብለዋል። በዚህም በ10ሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ለመማር ፍላጎት ላላቸውና በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችን የሚቀበል መሆኑን አስረድተዋል። እንደ አቶ መሀመድ ገለጻ ከዚህ ቀደም በየካቲት 12(እቴጌ መነን) ትምህርት ቤት ትምህረታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ከፈረንሳይ፣ ከሽሮ ሜዳና ከቀጨኔ አካባቢ የሚመጡ ናቸው። በአሁኑ ሰአትም ከ11ኛ ወደ 12ኛ ክፍል የተሸጋገሩ ተማሪዎችን በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኙ ትምህርት ቤቶች የማዘዋወር ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ከቀጨኔ አካባቢ የሚመጡ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ወይዘሮ ቀለመወርቅ ትህምርት ቤት፣ የፈረንሳይ አካባቢ ተማሪዎች ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ እንዲሁም የመነንና ሽሮ ሜደ አካባቢ ተማሪዎችን ደግሞ ወደ እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት የማሸጋሸግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ትምህርት መስጠት ሲጀምር ከ9ኛ እስከ 12 ክፍል ላሉ ሴት ተማሪዎች ትምህርት የሚሰጥ ይሆናል። ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ገብቶ ለመማር ት የ8ኛ ክፍል ውጤታቸው 75 እና ከዛ በላይ የሆነ እንዲሁም የ10ኛ ክፍል ውጤታቸው ደግሞ ከ3 ነጥብ 75 በላይ መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን መስፈርቱን ለሚያሟሉ ተማሪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገልጿል።