ቀጥታ፡

አገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግር ነው ተባለ

አዲስ አበባ ጳጉሜን 4/2011  አገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና  የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። የኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ በተመለከተ ለዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች በተባበሩት መንግስታት ደርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ገለጻ ተደርጎላቸዋል። በዚሁ ማብራሪያ ላይ የተገኙት ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው የአፍሪካ አገሮች ተርታ ለማሰለፍ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀደም ሲል በተደጋጋሚ በአገሪቷ ሲታይ የነበረውን የማይክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ለማስተካከልና ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አስረድትዋል። ማሻሻያው ኢትዮጰያን ወደ ብልጽግና የሚያሸጋገር መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጤታማነቱ የልማት አጋሮችን ድጋፍ ጠይቀዋል ብለዋል። በውይይቱ የተሳተፉ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችን አገሪቷ ድህነትን ለመቀነስና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል። የማሻሻያው አንዱ አቅጣጫ የመንግሥትን እጅ በመቀነስና የግል ዘርፉን ተሳትፎ በመጨመር መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና በሂደት መቀነስ ያስችላል ተብሎ ይታመናል። በኢትዮጵያ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተለይም በአቅርቦት በኩል የሚታየውን ጎደሎ ያስችላልም ተብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም