ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ዓመት ሲያከብሩ ህጻናትና ጧሪ ያጡ ወገኖችን እንዲያስቡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጥሪ አቀረቡ

ጷጉሜ 3/2011 ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ዓመት ሲያከብሩ ህጻናትን ጨምሮ ሰብሳቢና ጧሪ ያጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲያስቡ ጥሪ አቀረቡ። ህጻናትና ጨምሮ ከ22 ሺህ የሚልቁ በጎዳና የሚኖሩ ዜጎችን በመሰብሰብ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። ፕሬዚዳንቷ መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከዘጠኝ የህጻናት ማሳደጊያ ተቋማት ለተውጣጡ ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች በብሄራዊ ቤተ-መንግስት የምሳና መዝናኛ መርሃ ግብር አከናውነዋል። በማሳደጊያዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ፣ በዚህም እጣ ፈንታቸው የጎዳና ህይወት የነበረ እንደዚሁም የተለያየ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴት ህጻናት  ይገኙበታል። ህፃናቱ ከምሳ ግብዣ ባሻገር በቤተ መንግስት ቅጥር ጊቢ እንዲዝናኑ የተደረገ ሲሆን፤ የተለያዩ ስጦታዎችም ተበርክቶላቸዋል። በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ማስታወስ ለመጪዋ ኢትዮጵያም ጭምር ተስፋ ያለው ትውልድ መፍጠር በመሆኑ ሁሉም ሊያስባቸው እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ድጋፍ የሚሹ እጅግ በርካታ ህጻናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ችግሩን ለመቀነስ የመላው ህዝብን ያላሰለሰ ርብርብ ይጠይቃልም ብለዋል። በመሆኑም ዜጎች ህጻናቱን ሰብስበው በሚያሳድጉት ተቋማት በኩልም ይሁን በተለያየ መንገድ ከትንሽ ጀምሮ በአቅማቸው መጠን የበኩቸውን ማበርከት ይችላሉ፤ "ከአቅም በላይ የሆነ ችግር የለብንም" ሲሉም ገልፀዋል። በተለይም መጪውን አዲስ ዓመት ጨምሮ የመሳሰሉ ክብረ በዓላት ወቅት እነዚህን የህብረሰተብ ክፍሎች በማስታወስ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። በተለይም ህይወታቸውን በጎዳና የሚገፉ፣ በህመም ምክንያት በየሆስፒታል አልጋ ላይ የሚገኙና በየማሳደጊያው የሚኖሩ ህጻናትን እንደዚሁም ጧሪ ያጡ አረጋዊያንን በመጎብኘት 'ከጎናችሁ ነን፤ አለንላችሁ' ማለት ይገባል ብልዋል። የወገን አለኝታ ከምንም በላይ ትርጉም ስለሚኖረው ህዝቡ ይህንን በማድረግ የነገዎቹን ልጆች ተስፋ ማለምለም ይጠበቅበታልም ብለዋል። ዋናው ቁም ነገር ግን ህጻናቱ አገር ተረካቢ መሆን ይችሉ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍና እንክብካቤ በመስጠት ሌላው የሚያገኘውን ዓይነት እድል ማመቻቸት ነው ብለዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አሳዳጊ ያጡ ህጻናትን በመሰብሰብ የሚቻለውን ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ተቋማት ጥቂቶች መሆናቸውን ገልፀዋል። ከዚህ አንፃር በመላ አገሪቷ ህይወታቸውን በጎዳና የሚገፉትን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚያሻቸው ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው። የህጻናት ማሳደጊያ በማቋቋም አገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ተግባሩን የጀመሩት  በራሳቸው አቅም ተነሳስተው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ኤርጎጌ ሌላውም ዜጋ በየፊናው ተመሳሳይ ዓላማ ያለውን ተግባር ለመፈፀም ቢጥር ችግሩን መቀነስ ይቻላል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ህጻናትን ጨምሮ ህይወታቸውን በጎዳና ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከጎዳና በመሰብሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ሚኒስትሯ በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ በሚገኙ 11 ትላልቅ ከተሞች የተካሄደ ጥናትን ተከትሎ ህጻናትን ጨምሮ ከ22 ሺህ የሚልቁ የጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎች ተለይተዋል። ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የተቀረፀው ፕሮጀክት ትግበራ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ በይፋ የሚጀመር መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ በ2012 ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በተቀሩት ከተሞች ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል። በፕሮጀክቱ መሰረት በከተሞቹ የተለዩት 22 ሺህ የሚልቁ ዜጎች ከጎዳና መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የሚቋቋሙበትን መንገድ ለመዘየድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የሚከናወን መሆኑንም ገልፀዋል። ከህጻናትና ጎዳና ተዳዳሪነት ባሻገር የአረጋዊያን የኑሮ ሁኔታም ሌላው በኢትዮጵያ የሚስተዋል ማህበራዊ ችግር መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል። በዚህ ረገድ ያለውን ችግር መቀነስ ይቻል ዘንድም በመጪው መስከረም 2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ኃብት የማሰባሰብ ሥራ ለማከናወን ታቅዷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም