ቀጥታ፡

ጆፌ አሞራዎች የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነባቸው ተገለጸ

አዳማ  ጳጉሜ 03/2011  ዝሪያቸው የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው የጆፌ አሞራዎችን ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ። በዱር እንስሳትና አእዋፍ ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ሰራተኞች(ስካውቶች) በጆፌ አሞራ እንክብካቤ፣ መለየት፣ ጥበቃና ምዝገባ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በባለስልጣኑ የእንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ዳይሬክተር አቶ ግርማ ቲመር እንዳሉት  የጆፌ አሞራዎች ዝርያ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል። ዝሪያቸውን ለመታደግ  ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀባጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ጆፌ አሞራ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል። የሞቱ የቤትና የዱር እንስሳትን በማስወገድና በአካባቢ ፅዳት ጭምር አስተዋጽኦ ከሚያደርጋቸው መካከል ይገኝበታል። የጆፌ አሞራዎች በስፋት የሚገኙት በአዋሽና አዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርኮች በመሆኑ በፓርኩየሚገኙ የጥበቃ ሠራተኞች በአሞራዎች እንክብካቤ፣መለየት ፣ጥበቃና ምዝገባ ላይ በቂ እውቀት አግኝተው ዝርያቸውን ከጥፋት ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በአፍሪካ ካሉ  አስራ አንድ የጆፌ አሞራ ዝሪያዎች ውስጥ ስምንቱ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአእዋፍና ስነ ምህዳር ተመራማሪ ዶክተር ብሩክታዊት አብዱ ናቸው። በኢትዮጵያ ከሚገኙት ስምንቱ የጆፌ አሞራ ዝሪያዎች መካከል ስድስቱ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው። “በትላልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ላይ በማረፍ በብዛት በኤሌክትሪክ አደጋ እየሞቱ መሆኑን በጥናት አረጋግጠናል ” ብለዋል። በተጨማሪም በመርዝ የሚሞቱ የቤትና የዱር እንስሳቶችን በተለይም ውሻ፣ጅብና ሌሎችንም ስለሚመገቡ ሌላው ለጉዳት የዳረጋቸው ችግር ነው። “ይህን ችግር ለመፍታት  በመርዝ የሚሞቱ የቤትና የዱር እንስሳትን ጉድጓድ ቆፍሮ መቅበር ላይ ስካውቶችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ አለብን “ብለዋል። በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችንና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ፒላስቲክ እንዲሸሸፈኑ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መብራት ኃይል ጋር መሰራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። በስልጠናው ከተሳተፉት ስካውቶች መካከል አቶ ጌታቸው ዑራኤል በሰጡት አስተያየት “ስለ ጆፌ አሞራ የነበረን ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ምንም ዓይነት እንክብካቤና ጥበቃ አናደርግላቸውም ነበር “ ብለዋል። በአሁኑ ወቅት አካባቢን ከብክለት ከመጠበቅና ሥነ ምህዳርን ፅዱ ከማድረግ አንፃር ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ከስልጠና መገንዘባቸውን ተናግሯል። በቀጣይነት በጆፌ አሞራ እንክብካቤ፣መለየት፣ጥበቃና ምዝገባ ላይ በትኩረት በመስራት አእዋፉን ከመጥፋት አደጋ ለመጠበቅ ጥረት አንደሚያደረግም አመልክተዋል። ለሶስት ቀናት በተሰጠው ስልጠና ከአዳጌ አሰቦትና አዋሽ ብሔራዊ ፓርኮች የተወጣጡ የዱር እንስሳት የጥበቃ ሰራተኞች( ስካውቶች) ተሳትፈዋል። ስልጠናውን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ከአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር  ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም