የነገሌ ሀይማኖት አባቶች በአዲሱ አመት የሰላምና የአብሮነት እንዲሆን በጋራ እንሰራለን አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የነገሌ ሀይማኖት አባቶች በአዲሱ አመት የሰላምና የአብሮነት እንዲሆን በጋራ እንሰራለን አሉ
ጳግሜ 3/2011 አዲሱ አመት የአብሮነት፣ የሰላምና የልማት እንዲሆን ህዝብን በማስተማር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የነገሌ የሀይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡ የከተማው ነዋሪ ቀሲስ መለሰ ነጋ ''አዲሱ አመት ራሳችንን ከቂም፣ ጥላቻና በቀል በማራቅ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለስራና ለእድገት የምንረባረብበት መሆን ይኖርበታል'' ብለዋል፡፡ ወንድም ወንድሙን በማጥቃትና በመዝረፍ የሚገኝ ትርፍ ከፈጣሪ የሚያርቅ መጥፎ ተግባር በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጥላቻና ቂም በቀል እንዲቀር ለምእመናን በምንሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ትኩረት በመስጠት ለሀገሪቱ ሰላምና ገጽታ ግንባታ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ የነገሌ መካነየሱስ ቤተክርሲያን የሀይማኖት መሪ ፓስተር ቴዎድሮስ ነጋሽ አዲሱ አመት የሰላምና የአብሮነት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መክረዋል፡፡ ዓለም ያደነቀውን የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የመደጋገፍና የወንድማማችነት ባህላዊ እሴት ተጠብቆ ለመጭው ለትውልድ እንዲተላለፍ በአዲሱ ዓመት ቤተክርስቲያናቸው ምእመናንን በማስተማር የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግረዋል፡፡ ''አብሮነታችን እንዲጎለብትም መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር፤ የሀይማኖት ተቋማት ደግሞ ተከታዩቻቸውን በማስተማር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል'' ብለዋል፡፡ የጉጂ ዞን ሸሪአ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የነገሌ እስልማና ሀይመኖት መሪ ሸህ ከድር አብዱረህማን ''የሰላም ጥቅም የሚታወቀው ሰላም ሲጠፋ ብቻ ነው'' ብለዋል፡፡ ''በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎችን ከማፈናቀል እስከ እምነት ተቋም ማፍረስ የደረሰው የሰላም እጦት ዳግም እንዳይከሰት ችግሩን በይቅርባይት ልንሻገር ይገባል'' ብለዋል፡፡ ከመረዳዳት ባሻገር ወንድም ወንድሙን በመግደል ያልተገባ ስልጣን ለመያዝና የራስ ያልሆነ ሀብት የማፍራት ሀሳብም ሆነ ምኞች በፈጣሪ ቃል ቅዱስ ቁርአን የተከለከለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ አመት የህግ የበላይነት የሚከበርበት እርስ በርስ የምንረዳዳበት የአብሮነት፣ የሰላምና የልማት እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡