ቀጥታ፡

ብሔራዊ የኩራት ቀን አገራዊ ታሪክ፣ የባህልና የጀግንነትን በሚያሳዩ ትእይንቶች ተከበረ

አዲስ አበባ  ጷጉሜ 3/2011  ብሔራዊ የኩራት ቀን የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ፣ ባህልና ጀግንነት በሚገልጹ ትዕይንቶች በአዲስ አበባ ተከብሯል። እለቱ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሲከበር በአገራዊ ኩራትነት ከሚጠቀሱት መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች፣ የአገር መከላከያና የፖሊስ አባላት በስፍራው በመገኘት አድምቀውታል። የአገሪቷ ታሪካዊ ቅርሶችም በትእይንትነት ቀርበው በጋራ አገራዊ ኩራትነታቸው ተወስተዋል። የኢትዮጵያ ታላቅ የኩራት ምንጭ በመሆን በዓለም አደባባይ ከጥንት እስከዛሬ ሰንደቋን ከፍ በማድርግ የሚታወቁት አትሌቶቿም የትእይንቱ አካል ነበሩ። በተለያዩ የሙያ መስኮች አገራቸውንና ህዝባቸውን ያሰገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ ዜጎችም በኩራትነት ተወስተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በእለቱ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በርካታ የኩራት ተምሳሌቶች እንዳሏት ጠቅሰዋል። እለቱ በአዲስ አበባ መከበሩ ከተማዋ ነዋሪዎቿን በእኩለነት የምታስተናግድ ምቹና የሁሉም ኩራት መገለጫ መሆኗን የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል። በአዲስ አበባ በተከበረው ብሄራዊ የኩራት ቀን ከ250 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም