በበዓል ገበያው የእህል ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ እንዳለው ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በበዓል ገበያው የእህል ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ እንዳለው ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ
ጳጉሜን 3/2011 በበዓል ገበያ የእህል ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ቢያሳይም ቀደም ካሉት ግዜያት ጋር ሲነጻጸር የተጋነነ አለመሆኑን በአዲስ አበባ አስተያየታቸውን የሰጡ ነጋዴዎችና ሸማቾች ይናገራሉ፡፡
የኢዜአ ሪፖርተር ጥቂት ቀናት የቀሩትን የአዲስ አመት በዓል የእህል ገበያን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ለበዓሉ ቅድመ ዝግጅት የተለያዩ የእህል አይነቶችን ሲሸምቱ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች የእህል ዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም የተጋነነ አይደለም ይላሉ።
በተደረገው የገበያ ቅኝት ጤፍ ከ31- 35 ብር፣ ስንዴ ከ21-22 ብር፣ አተር 33 ብር፣ ባቄላ 32 ብር፣ ቦቆሎ 14 ብር በኪሎ እየተሸጠ ማየት ተችሏል።
ወይዘሮ ስንዱ አብተው ለመጭው የአዲስ አመት በዓል ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረው የጤፍ ዋጋ ከበዓል በፊት ከነበረው ጭማሪው የተገናነ አለመሆኑን ተናግረው፤ ጤፍ የእለት ተእለት ፍጆታ በመሆኑ በየጊዜው የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ግን እንደሚያሳስባቸው ይገልጻሉ፡፡
ስንዴ ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ መስታወት ቦጋለ በበኩላቸው ከአንድ ወር በፊት የነበረው የስንዴ ዋጋ የአራት ብር የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የጠቀሱት።
“ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” የሚሉት ወይዘሮ መስታወት ለበዓል ከአቅም በላይ በመደገስ ለአላስፈላጊ ወጭ መዳረግ ተገቢ እንዳልሆነም ገልጸዋል።
በእህል ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ አስማማው ተመስገን በበኩላቸው ወቅቱ ምርት የሚሰበሰብበት ባለመሆኑ የምርት አቅርቦት በመቀነሱ የእህል ገበያው የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ የሚጠበቅ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
የበዓል ሰሞን እንደ ሌሎች የፍጆታ ምርቶች የእህል ምርት ብዙም እንደማይፈለግ የተናገሩት አቶ አስማማው፤ የዋጋ ጭማሪው ከምርት አቅርቦት እጥረት ብቻ ሳይሆን ትራንስፖርት ችግርና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች እንዳሉትም ይገልጻሉ።
የተሻለ የምርት አቅርቦት የሚኖረው በበጋው ወራት መሆኑን ሚናገሩት ሌላው የእህል ነጋዴ አቶ አዲሱ ፋንታ አሁን ያለው የእህል ዋጋ ጭማሪ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያዥነት እንዳለው ነው የጠቀሱት።