ቀጥታ፡

ማህበረሰቡ ሰላምን ለማስጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

ባህር ዳር  ኢዜአ ጳጉሜ 2/2011 ሁሉም ማህበረሰብ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ። "እኔ ሰላማዊ ነኝ!! ባህርዳርም የሰላም ከተማ ነች!!" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ህዝባዊ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ በውይይቱ ወቅት አንዳሉት ሁሉም ማህበረሰብ ለራሱና ለአካባቢው ድህንነትና ልማት መኖር ሰላም ወሳኝ ነው። እየተገባደደ ባለው ዓመት  በከተማው የተለያዩ መጥፎ ክስተቶች ቢጋጥሙም በህዝቡ አርቆ አሳቢነት፣ አስተዋይነትና የመረጋጋት መንፈስ በፍጥነት ወደ ነበረበት ሰላም መመለስ መቻሉን አመልክተዋል። ለዚህም የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች አሰተዋጽኦ ማድረጋቸወን ጠቅሰው "በቀጣይም ሰላምን በማስጠበቅ ከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ መዳረሻ  ለማድረግ ቅድሚያ ለሰላም መሰጠት አለበት "ብለዋል። የሀገሪቱ ባለሀብቶችና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሰላም ከተማ ወደ ሆነችው ባህርዳር መጥተው በልማቱ እንዲሳተፉ የከተማው አስተዳደር  ትብብር እንደማይለቻው አስታውቀዋል። የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ወራት በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መጣቱን ገልጸዋል። ይህም በመጪው አዲስ ዓመት በክልሉ የሚገኘውን የጸጥታ አካላትን በማጠናከር የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ አቅም ሆኖ እንደሚያገልግል ተናግረዋል። ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቁመው የኃማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ጋዜጠኛና የፍልስፍ ባለሙያ  ቤተልሄም ለገሰ ባደረገችው አነቃቂ ንግግር "ሰላም ለግለሰብ የውስጥ አካሉ ጤንነት ለማህበረሰብ ደግሞ የመፈቃቀር፣ የመተሳሰርና የአንድነት ገመድ ነው" ብላለች። አንድ ሰውም ሆነ ማህበረሰብ ምንም እንኳ ምጡቅ አእምሮ፣ እውቀትና የልህቀት አስተሳሰብ ቢኖረውም አውጥቶ ለሀገር ብልጽግና ጥቅም ላይ ማዋል የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ እንደሆነ ተናግራለች። እንኳን ለሰው ልጆች ለምድር ፍጥረታት ሁሉ ሰላም ይሁን እያለች ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ እንደምትጮህ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባህርዳር ሃገረ ስብከት ተወካይ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ናቸው። አርሶ አደሩ አርሶና ዘርቶ ለማምረት፣ ነጋዴው ነግዶ ለማትረፍና ለሌላም ሰላም የመጀመሪያው ምዕራፍ በመሆኑ ሁሉም ለዚህ ዘብ መቆም እንዳለበት መክረዋል። በውይይት መድረኩ  ስለ ሰላም የሚሰብኩ የመነባንብ፣ ግጥም፣ ሙዚቃና ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎች ቀርበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም