ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት የሀገርና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ይበልጥ ዝግጁ መሆናቸውን የምስራቅ ዕዝ የሠራዊቱ አባላት ተናገሩ

ሐረር (ኢዜአ) ዻጉሜን 2 ቀን 2011--በአዲሱ ዓመት የሀገሪቱን ሉአላዊነት በማስከበር የሀገርና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀታቸውን በምስራቅ ዕዝ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት ተናገሩ። የሠራዊቱ አባላት እንዳሉት ለህገመንግስቱ ፍፁም ታማኝ በመሆን ሀገርንና ህዝብን ከውስጥና ከውጪ ወራሪ ኃይል ለመጠበቅ ቁርጠኛ ናቸው። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሠራዊቱ አባላት መካከል ሻለቃ መጋቢ ባሻ ደምለው ተፈራ እንደተናገረው ሠራዊቱ የሚገጥሙትን ችግሮች በማለፍ ህገ መንግስቱና የህዝብ ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የታዩ አንዳንድ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ በመመከት ሀገሪቱንና ዜጎችን ከጥቃት መከላከል እንደቻለም ተናግረዋል፡፡ “አላማዬም ተልዕኮዬም ሀገርንና ህዝብን መጠበቅ ነው፤ በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ፣ አስተሳሰብና ራዕይ ተልኮዬን በቁርጠኝነት ለመወጣትና የህዝብን ሰላም ለመጠበቅ ተዘጋጅቺያለሁ” ሲልም ገልጿል፡፡ "ከውስጥም ይሁን በውጭ ኃይል የሚነሱ የፀጥታ ችግሮችን ለመከላከል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ያሉት ደግሞ ሌተናል ኮሎኔል አክሊሉ አበበ ናቸው። የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ከወጣቱ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር ሆነው ባከናወኑት የመከላከል ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። በዓሉን አስመልክተው የሰራዊቱ አባላት የጽዳት፣ የደምልገሳና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን ማከናወናቸውን ጠቁመው " በአዲሱ ዓመት ለቆምነለት ዓላማ ይበልጥ ተግተን እንሰራለን" ብለዋል። "በአካባቢው ከወሰን ጋር ተያይዞ አለመግባባቶች ሲከሰቱ በማረጋጋት ሥራና በተለያዩ ሀገራዊ የበጎ አድራጎት ተግባራት ስንሳተፍ ቆይተናል" ያለችው ደግሞ ምክትል አስር አለቃ የሺሀረግ አለነ ናት። “ከባንዲራዬ ስር ቃል የገባሁት ሀገሬንና ህዝቦቿን ለመጠበቅ ነው፤ በመሆኑም ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን አገሬንና ህዝቦቿን ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ ነኝ” ስትል ተናግራለች፡፡ ሠራዊቱ ከህዝብ የወጣና ለህዝብ የቆመ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ ያለው ፍቅርና ድጋፍ የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አመልክታለች፡፡ "በዓመቱ ያጋጠሙንን ችግሮች በትጋት ለማለፍ ስንንቀሳቀስ ቆይተናል" ያለው ደግሞ ወታደር አክመል ኑር ነው። በአዲሱ አመትም ለህገመንግስቱ ፍፁም ታማኝ በመሆን ሀገርንና ህዝብን ከየትኛውም ጠላት ለመጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፤ ለእዚህም ህዝቡ ከጎናቸው እንዲቆም ነው የጠየቀው። የምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ዱባለ አብዲ በበኩላቸው እንዳሉት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ  በሠራዊቱ አባላት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል። ለዚህም ሠራዊቱ በሐረሪ ክልል በከተማና በገጠር አካባቢዎች የፅዳት ዘመቻ ማካሄዱን፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደሱን እንዲሁም በደም ልገሳና በችግኝ ተከላ ተግባራት መሳተፉን ተናግረዋል፡፡ ጀነራል ዱባለ እንዳሉት ሠራዊቱ በዓሉን አስመልክቶ ጠቃሚ ሥራዎችን ማከናወኑ በህብረተሰቡና በሠራዊቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ያበለጠ ያጠናክረዋል፡፡ የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ጳጉሜን 4 ቀን 2011 ዓ.ም እንደ ተቋም በምስራቅ እዝ አዘጋጅነት በሐረር ከተማ እንደሚከበር ለማወቅ ተችሏል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም