የንግዱ ማህበረሰብ ከውጭ ምንዛሪና ህገ ወጥ አሰራር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ከመንግስት ጋር ሆኖ መፍታት ይጠበቅበታል ተባለ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከህገ ወጥ የንግድ አሰራር ጋር በተያያዘ በሀገሪቷ ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ ላይ እያጋጠመ ያለውን ችግር መፍታት  የሚቻለው መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ በቅንጅት መስራት የሚችሉበትን አሰራር በመዘርጋት አንደሆነ  ተገለፀ። ይህ የተገለፀው ብሄራዊ የፕላን ኮሚሽን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ሂደት ላይ በመከረው ውይይት ላይ ነው። የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ምሁራንና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በታደሙበት ስብሰባ ላይ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ  ያለፉት ዓመታት አፈፃፀም ችግሮችና በቀሪዎቹ ዓመታት ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባሉ በተባሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ኃብት መምህር ዶክተር  ታደለ ፈረደ ለውይይቱ መነሻ ባቀረቡት ፅሁፍ  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የእስካሁኑ አፈጻጸም ደካማ መሆኑን አብራርተዋል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን ያነሱ ሲሆን በዋነኛነት ያተኮሩት ግን የግብርናው ዘርፍ ላይ የሚጠበቀው ለውጥ አለመምጣቱን ነው። የግብርናው ዘርፍ እድገት አለማምጣቱ በኢንዱሰትሪው ልማት ላይም ተፅእኖ ማሳደሩን የሚናገሩት ዶክተር ታደለ፤ ግብርናው በውጭ ገበያ ላይ መወጣት የሚገባውን ሚና አየተጫወተ አይደለም ብለዋል። የግብርና ምርታማነት በዓይነትም ሆነ በጥራት አለመጨመሩንም ባለሙያው ጨምረው  ተናግረዋል። "የውጭ ንግድን በተመለከተ በመጀመሪያውም  ሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ችግሮች አሉ" ያሉት ተመራማሪው፤ ሀገሪቷ አሁንም ድረስ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የግብርና ምርቶችን ብቻ ነው በማለትም ገልፀዋል። በቀሪዎቹ የእቅዱ ዓመታት ለመስኖ ልማት፣ ለመካከለኛና ሰፋፊ እርሻዎች አንደዚሁም የወጪ ንግድን ለማጠናከር የሚያስችሉ የአደረጃጀትና የመዋቅር ለውጦችን ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። መንግስት በሀገሪቷ የሚታቀዱትን የልማት ስራዎች በብቃት ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገቢ ከመሰብሰብ አኳያ ድክመት እንዳለባትም አመልክተዋል። በንግዱ ማህበረሰብ በኩልም  በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ የማይከፍሉ እንዳሉ ገልፀዋል።  ይህም በገቢ አቅም ላይ ችግር ሆኗል ነው የተባለው። የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው ሁለተኛው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ ለውጥ አላመጣም ማለት ባይቻልም የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ተናግረዋል ። የሀገሪቷ 70 በመቶ በላይ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የግብርናው ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ይናገር፤ ዘርፉን ለማሳደግ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣትን ይጠይቃል ብለው፤ ሆኖም በዚህ ረገድም የተከናወኑት ተግባራት የሚያበረታቱ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል። ከቀበሌ ጀምሮ አስከ ላይ ድረስ ያለው አመራር እንደዚሁም የተለያዩ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች ላጋጠሙት ፈተናዎች አንደ ችግር ተቀምጠዋል። ለአብነትም ለግብርና ምርትና ምርታማነት ቁልፍ የሆነው የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረና አሁንም ድረስ በሚመለከተው አካል ሊፈታ ያልቻለ መሆኑን በመጥቀስ። በግሉ ዘርፍ በኩል የሚታዩ ጉድለቶችም ለተጠቀሱት ችግሮች አንዱ መንስኤ መሆኑም ተመልክቷል። ዶክተር ይናገር ግብርን ከመደበቅ ጀምሮ ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተብለው በመንግስት የሚሰጡ አድሎችን በመጠቀም በውጭ ምንዛሪ ከቀረጥ ነፃ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ በርካቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። ዶክተር ይናገር እንደሚሉት ከውጭ ምንዛሬም ሆነ ከመንግስት ገቢ ማነስ ጋር በተያያዘ የሚታዩትን ችግሮችንም ለመፍታት መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተባብረው መስራት አለባቸው። በመንግስት በኩል ደግሞ በአሰራር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መድፈን ይገባል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለይም ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጡ ማበረታቻዎች በአግባቡ ለሚፈለገው ዓላማ መዋላቸውን መከታተልና መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል። በወደቦች አካባቢ ያለው የሎጂስቲክስ አገልግሎት የተቀላጠፈ አለመሆንና አሰራሩም ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ መሆኑንም የስብሰባው ተሳታፊዎች አመልክተዋል። ይህም ሀገሪቷ በተለይ ለውጭ በምታቀርበው እቃ ተወዳዳሪ እንዳትሆን እያደረጋት በመሆኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ተብሏል። ኮሚሽነሩ እንዳሉት የዚህ ዓይነት መድረኮች ከሚመለከታቸው ሌሎች የተለያዩ አካላት ጋርም በመካሄድ ላይ ነው። የስብሰባው ዓላማ በትግበራው ላይ የሚታዩትን ችግሮች በማየት ወደፊት በምን ዓይነት መንገድ መቀጠል ይገባል የሚለውን ለመለየት ነው ተብሏል። በቅርቡም ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ትግበራ አፈፃፀምን በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሰፊ ጉባኤ የሚጠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም