የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከሌሴቶ አቻው ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከሌሴቶ አቻው ጋር ይጫወታል
ጳጉሜ 2/2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እ.አ.አ በ2022 በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከሌሴቶ አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል። በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የሚደረገው የአፍሪካ አገሮች የማጣሪያ ጨዋታ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን የመልስ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ። በአሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታው ነገ 20 ሺህ ተመልካቾችን በሚያስናግደው ሴትሶቶ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ከሌሴቶ አቻው ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል። ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ 0 ለ 0 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ዋልያዎቹ ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ወደ ስፍራው ያቀና ሲሆን ትናንት በልምምድ ወቅት እክል እንደገጠማቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል። ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታው በሚደረግበት ስታዲየም ልምምድ ሊያደርግ ሲል "መብራት ሆን ብሎ ጠፍቶ" በስታዲየሙ ለነበሩ ሰዎች መብራቱ እንዲበራላቸው ቢጠይቁም የሚመለከታቸው አካላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቡድኑ በጨለማ ልምምዱን ለመስራት መገደዱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ዋልያዎቹ ከተጋጣሚው በኳስ ቁጥጥር የጨዋታ ብልጫ ወስዶ ቢጫወትም ለግብ የቀረቡ እድሎችን መፍጠር ያልቻለ ሲሆን የፊት መስመር ተጫዋቾች የጨራሽ አጥቂ ባህሪ የሌላቸው መሆኑ በምክንያትነት መጠቀስ ይቻላል። አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በጨዋታው ላይ የታየውን የአጥቂ መስመር ክፍል በማረም በመልሱ ጨዋታ ውጤት ይዞ ለመውጣት ቡድናቸው እንደሚጫወት ገልጸዋል። ዋልያዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በማጥቃት መስመር ላይ ያለበትን ድክመትን መቅረፍ የሚጠበቅበት ሲሆን የኳስ ቁጥጥሩንም ወደ ግብ እድሎች መቀየር ይኖርበታል። በ38 ዓመቱ ደቡብ አፍሪካዊ አሰልጣኝ ታቦ ሴኖንግ የሚመራው የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ስልት የተጫወተ ሲሆን ከክንፍ መስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም በዋልያዎቹ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ታይተዋል። በጨዋታው ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተሻለ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን የቡድኑ አጥቂዎች ያገኙትን የግብ እድል መጠቀም አለመቻላቸው እንደ ድክመት የሚነሳ ጉዳይ ነው። በቅጽል ስማቸው አዞዎቹ በመባል የሚጠሩት ሌሴቶዎች በመጀመሪያው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን የግብ እድል ያለመጠቀም ችግር በመቅረፍና ጫና ፈጥሮ በመጫዋት ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንደሚጫወቱ ቡድኑን ከተረከቡ ሁለት ሳምንት ያልሞላቸው ታቦ ሴኖንግ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ሌሴቶን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር ማሳለፍ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።