የጋሞ አባቶች ሰላምና መቻቻልን ለማስቀጠል ያላቸውን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞ አባቶች ሰላምና መቻቻልን ለማስቀጠል ያላቸውን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ
አርባምንጭ ኢዜአ ጳጉሜ 2/ 2011፡-የጋሞ አባቶች ሰላም ፣ ፍቅርና መቻቻልን ለማስቀጠል ያላቸውን ተሞክሮ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ፡፡ ብሔራዊ የሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ አባቶች እንዳሉት ምሳሌነታቸው ለኢትዮጵያዊ አንድነት ጉልህ ድርሻ ያለው ነው። ከጋሞ አባቶች መካከል አቶ ሰዲቃ ስሜ በሰጡት አስተያየት በሰው ልጆች መካከል ግጭቶች መከሰቱ ተፈጥሮዊ ባህሪ ቢሆንም ግጭት እንዳይከሰት ከተከሰተም በቀል የሌለው እርቅ መፈጸም የቆየ ባህላዊ ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰዲቃ እንዳሉት በማህረሰቡ መካከል ግጭት ቢከሰት “ኦጋዳ” የሚባሉ የህዝቡ አምባሳደሮች “ዱብሻ” በተሰኘው ፍትህ አደባባይ በመቆም በበዳይና ተበዳይ መካከል ቂም አልባ እርቅ በመፈጸም ጋሞዎች ጠንካራ ባህላዊ እሴት ገንብተዋል፡፡ “የአባቶችን ምክርና ተግሳጸ ተላልፎ ጥቃት ለመፈጸም የሚቃጣ ቢኖር ከህዝቡ የሚገለል በመሆኑ ቂመኝነት በጋሞ ምድር አይታሰብም ብለዋል፡፡ የጋሞዎች ምድር የኢትዮጵያ እንደመሆኑ በአከባቢዉ ካሉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ተከባብረውና ተቻችለው ያለልዩነት ለዘመናት መኖራችን አመልክተዋል፡፡ “ለኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ ምድር እንግዳ ሊሆን አይገባም “ ያሉት አቶ ሰዲቃ የጋሞዎችን የሰላም የፍቅርና የመቻቻል ልምድ ለሌሎችም ኢትዮጵያዊን ለማካፈል ዝግጁ እንደሆኑ ገልዋል። ለዚህም መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው አመልከተዋል፡፡ በህብረተሰቡ መካከል ግጭት ቢከሰት እንኳ አባቶች ተንበርክከው እርጥብ ሣር ከያዙ ሁለቱም ወገኖች ወድያውኑ ግጭቱን እንደሚያቆሙ የገለጹት ደግሞ ሌላው የጋሞ አባት አቶ አዳሙ ኪሮ ናቸው፡፡ “ባለፈው መስከረም ወር በቡራዩ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በአርባ ምንጭ ከተማ መሰል ችግሮች እንዳይከሰት የተደረገው ለባህሉ ተገዥ የሆኑ ወጣቶች በመፈጠራቸው ነው” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ለሰው ልጆች ሰላም ከምንም በላይ በመሆኑ ብሔራዊ የሰላም ቀን መከበሩ ለኢትዮጵያዊ አንድነታችን መልካም አጋጣሚ ነው ፡፡ ሰላምና መቻቻልን ለማስቀጠል ያላቸውን ተሞክሮ ወደ ሌለው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ለማካፈል ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል ከጋሞ ወጣቶች መካከል ሙሴ ከበደ በበኩሉ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ቢያስከትልም በጋሞ አከባቢ ሰላም እንደነበር አስታውሷል፡፡ ይህም የሚመክሩንና የምገስጹ አባቶች በመኖቸው እንደሆነ ጠቅሶ አባቶች ጠብቆዩትን ያቆዩትን ባህላዊ እሴት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡ “ሰላም ስለተመኘን ብቻ የሚረጋገጥ ጉዳይ ሳይሆን አባቶች ተገቢውን ሚና መጫወት ሲችሉ ነው “ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው። ለዚህም ጋሞዎች ግጭትን ማስቆም የሚያስችል ጠንካራ ባህላዊ እሴት እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡ መንግስትም የህግ የበላይነቱን ለማስከበር ከመቼውም በላይ መስራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል ፡፡ ለሰላምና መቻቻል መኖር ባላቸው ተሞክሮ የጋሞ አባቶች በኢትዮጵያ የ2011 የዓመቱ የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ እንደሆኑ ይታወቃል ፡፡