የካይዘን ፍልስፍና በመተግበር ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ከብክነት ማዳን ተቻለ - ኢዜአ አማርኛ
የካይዘን ፍልስፍና በመተግበር ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ከብክነት ማዳን ተቻለ
ጳጉሜ 2 /2011 የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በተጠናቀቀው የበጀት አመት የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ በማድረግ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወጪ ማዳን መቻሉን ገለፀ ፡፡ የኤጀንሲው የፕላን ክትትልና እቅድ ግምገማ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉወርቅ ሰጠኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ በመላ ሀገሪቱ በስሩ ከሚገኙ 19 ቅርንጫፎች መካከል በሃዋሳና በመቀሌ ቅርንጫፎች የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የካይዘን አሰራር ተግባራዊ በሆነባቸው በሁለቱም ቅርንጫፎችም ለሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር ሙሉ ጊዜያቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ በማድረግ ተነሳሽነትን ማሳደግ ተችሏል ፡፡ ለአሰራርና ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ያልሆኑ ቢሮዎችን በመለየትና መልሶ በማደራጀት ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በተሰራው ስራ የአገልሎት ቅልጥፍና ጥራት እንዲሻሻል ማስቻሉን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ። ለበርካታ ዓመታት በመጋዘኖች ያለአግልግሎት የተቀመጡ ንብረቶችን በመፈተሽ ፣ የተበላሹትን በማስወገድና ያልተበላሹትን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ አላስፈላጊ ብክነቶች ማስቀረት እንደተቻለ አስረድተዋል ። በካይዘን የስራ አመራር ፍልስፍና ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን በመተግበር በበጀት ዓመቱ ኪራይ የሚከፈልባቸውን 23 መጋዘኖች ወደ ሶስት ዝቅ እንዲሉ በማድረግ ውጤታማ ሆኗል ። በካይዘን ትግበራ ድምር ውጤት በተለይ ደግሞ ወጨን በመቀነስና ብክነትን በመከላከል 500 ሚሊዮን ብር ማዳን እንደተቻለ ከወይዘሮ ሙሉወርቅ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋትና ዘላቂነቱን በማረጋገጥ በአዲሱ ዓመት በ15ቱ ቅርንጫፎች ለመተግበር በሃዋሳ ፣ በመቀሌ ፣ በባህርዳርና በጅማ ቅርንጫፎች ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል ። በተጠናቀቀው በጀት አመት በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ 4 ሺህ 588 የመንግስት የህክምና ተቋማት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ማሰራጨቱን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።