ቀጥታ፡

ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ወጣቶች ለሠላም መስፈን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል- የአገር ሽማግሌዎች

ጳጉሜ 2/2011 በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ወጣቶች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ታሪክ ያለው፣ ኢትዮጵያም ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሣሌት ናት የሚሉት የኢትዮጵያ የአገር ሽማገሌዎች መድረክ አባል ሃጂ ኢሳ ሼህ ዑመር ናቸው። “ኢትዮያዊያን በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ተቻችለን ኖረናል” ያሉት ሃጂ ኢሳ ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቀውም ሉዓላዊነትን ስታስከብርና ዓለምን ስታስታርቅ መሆኑን ያወሳሉ። አሁን ላይ የሚስተዋለውን የእርስ በእርስ ግጭት ለማስወገድ ሁሉም ሰው ከግል ፍላጎቱ ይልቅ ለአገራዊ ሠላም መቆም እንዳለበት መክረዋል። የሠላም መጥፋትን መራራነት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ልመና ላይ ከሚገኙ ሶሪያዊያን፣ አንድ ሃይማኖትና ቋንቋ ኖሯቸው በመላው ዓለም ከሚሰደዱ ሶማሊያዊያን፣ የመናዊያንና ሊቢያዊያን መማር ይገባል ብለዋል። መንግስታዊ ስርዓት በጎና ደካማ ጎን አንደሚኖረው ገልጸው አንዱ ወደ ሌላው ጣት ከመቀሰር እንደ ደቡብ አፍሪካ ትናንትን በማለፍ መወያየትና አዲስ አገር መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለማርገብም የአገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ቀደም ሲል እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የአገር ሽማግሌዎች በተለይም በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት መሪዎች በሠዓታት ውይይት እንዲፈታ፣ በቀጣናው ሠላም እንዲመለስና የቀደሙ ግንኙነቶችና መስተጋብሮች እንዲቀጥሉ መደረጉን ለአብነት አውስተዋል። እናም በአሁኑ ወቅት ኃላፊነታቸውን የዘነጉ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን አገራዊ ሠላም ለማረጋገጥና ለነገ ልጆች የተሻለች አገር ለማስረክብ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። አቶ ኃይለሚካኤል ናና ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በመምህርነት፣ በሽግግር መንግስቱ ወቅት በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንዲሁም በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አርቃቂ አባልነት አገልግለዋል። በቀድሞ ስርዓተ መንግስታት ጨቋኝና ተጨቋኝ ሕዝብ እንዳልነበር የሚገልጹት አቶ ኃይለሚካኤል የገዥ መደብ እንጂ ሁሉም ሕዝብ ተጨቋኝ እንደነበር አንስተዋል። ‘ወላይታ የተወለድኩት በታሪክ አጋጣሚ እንጂ በምርጫ አይደለም’ የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል ኢትዮጵያዊያን በጋብቻ እስከ አምቻ የተሳሰሩና በተለያዩ ዘመናት የአሰፋፈር ሂደቶች የተሰባጠሩ እንደሆኑ ይገልጻሉ። "በሕገ መንግስቱ ፌዴራላዊ ስርዓት ስንመሰርት መናናቅን አስወግደን በአብሮነት ለመኖር፣ ራስን በራስ እያስተዳደርን እንድንኖር እንጂ ‘አንተ ከዚህ ኑር፣ አንተ ውጣልኝ’ ለመባባል አልነበረም" ይላሉ። የኢትዮጵያ ምሁራን ‘ከእኔ ወደ እኛ’ነት መለወጥ እንዳለባቸውና በቀድሞ ጊዜ የነበረውን ግብረገብነት ለወጣቶች ማስተማር እንደሚገባም አብራርተዋል። የኢትዮጵያ የአስተዳደርና ፍትህ ስርዓቶች ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ደግሞ ለአገራዊ ሠላም ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችና ዕውቀቶችን ያነሳሉ። አቶ አብዱልፈታህ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ህዝቦችን የፍትህና አስተዳደር ስርዓቶች በማጥናት ከ15 በላይ መጽሃፍትን ያሳተሙትና ሰሞኑን በተካሄደው የዓመቱ በጎ ሰው መርሃ ግብርም ተሸላሚ ናቸው። በጥናታቸው በየብሔረሰቡ የሚገኙ ግጭትን በባህላዊ መንገድ የመፍቻ ቁልፎችና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ባህላዊ የፍትህና የአስተዳደር ስርዓቶች በህግ እንዲታገዱ ተደርገዋል ይላሉ። እነዚህን ባህላዊ የአስተዳደርና የፍትህ ስርዓቶች በግብዓትነት መጠቀም ከተቻለ ዕውቀቶቹ ዛሬም ለሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች መፍትሄ እንደሚሰጡም ያምናሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም