ከሆስፒታል የተሰረቀችው ህፃን ከሁለት ቀናት ፍለጋ በኋላ ተገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ከሆስፒታል የተሰረቀችው ህፃን ከሁለት ቀናት ፍለጋ በኋላ ተገኘች

ጋምቤላ ኢዜአ ጳጉሜ 2/2011 ከጋምቤላ ሆስፒታል የተሰረቀች የአንድ ቀን ተኩል ዕድሜ ያላት ህፃን ከሁለት ቀናት ክትትል በኋላ ከነሙሉ ጤንነቷ ተገኘች ። የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡቲያንግ ኡቻን እንደገለፁት በጋምቤላ ሆስፒታል ነሀሴ 28 ቀን 2011 ዓም አንዲት ህፃን በሰላም ወደ ዓለማችን ተቀላቅላለች ። ከምጥ ጋር ታግላ ጤናማ ህፃን በሰላም የተገላገለችው እናት ድካሙ አልለቀቃትም ነበርና በማግስቱ አገር አማን ነው ብላ ጨቅላዋን አጠገቧ እንዳስቀመጠች እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋታል ። ከእንቅልፏ ስትነሳ ግን የአንድ ቀን ተኩል እድሜ ያላት የአብራኳን ክፋይ እንዳስቀመጠቻት ከጎኗ የለችም ።
እናት በድንጋጤ ተውጣ የድረሱልኝ ጥሪ በማሰማቷ የሆስፒታሉ ማህበረሰብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ስለ ጉዳዩ ማውረድ ማውጣት ይጀምራል ። ዋነኛው መፍትሔ ሆኖ የተገኘው ግን ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቅ ነበር ። የክልሉ ፖሊስም ነሀሴ 29 ቀን 2011 ዓም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ጠፋች የተባለችውን ጨቅላ ህፃን ለማግኘት ፍለጋውን ይጀምራል ። የክልሉ ፖሊስ ከሆስፒታሉ ባገኘው የመነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ለሁለት ቀናት ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ክትትል ህፃኗ በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 01 ተደብቃ ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ በአንድ ግለሰብ ቤት ተገኝታለች ። ኮሚሽነር ኡቲያንግ እንደገለፁት ህፃኗ ከነሙሉ ጤንነትዋ የተገኘች ሲሆን ፖሊስ ለወላጅ እናቷ አስረክባቷል ። ጨቅላዋን ሰርቃ ተሰውራለች የተባለችው ተጠርጣሪም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በምርመራ ላይ ትገኛለች ብለዋል ። የምርመራ መዘገቡ እንደተጠናቀቀ ተጠርጣሪዋ ለህግ እንደምትቀርብም ከኮሚሽነሩ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። አስገራሚው ነገር ግን እውነተኛዋ አራስም ሆነች በጨቅላ ህፃን ስርቆት ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ግለሰብ ከሁለት የተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የመጡ መሆናቸው ነው ። አራሷ በጤና ተቋም ለመውለድ ከጀዌ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የመጣችና ከወለደች በኋላም በሀኪሞች ክትትል ላይ የነበረች ስትሆን ህፃኗን የሰረቀችው ደግሞ ከጉኘል የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያ የመጣች ናት ተብሏል ። ለምን እንደመጣችና ህፃኗን ለምን መስረቅ እንደፈለገች በምርመራው የሚታወቅ ይሆናል ተብሏል ። የጋምቤላ የሆስፒታል ስራ አሰኪያጅ ተወካይ አቶ ኡጃይ ኡበኒ እንዳሉት ሆስፒታሉ ለእናትና ልጅ ተገቢውን ክትትልና የተሟላ የህክምና እንክብካቤ እያደረገላቸው ይገኛል ። ድርጊቱ በአሮጌው ዓመት ማብቂያ አካባቢ መፈፀሙ ደግሞ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም የሚለውን ብሂል እውነት አስመስሎታል ።
