ቀጥታ፡

የአስመጪና ላኪዎች ፈቃድና እድሳት በክልል ደረጃ መሰጠት ተጀመረ

ጳጉሜን 1 / 2011  (ኢዜአ) በፌዴራል ደረጃ ይሰጥ የነበረው የአስመጭዎችና የላኪዎችን የንግድ ፈቃድና ዕድሳት አሰጣጥ ወደ ክልሎች እንዲወርድ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ ያግዛል የሚል ተስፋ እንዳሳደረባቸው በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ገለጹ። የአስመጪነትና የላኪነት የንግድ ፈቃድና ዕድሳት በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር  ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል። በኢንዱስትሪ ምርቶች አስመጪነት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አዲስ ኪዳን ለኢዜአ እንደገለጹት አገልግሎቱ ወደ ክልሎች መውረዱ ለፈቃድና እድሳት ወደ አዲስ አበባ የምናደርገውን ምልልስ ያስቀራል ብለዋል ። ነገር ግን ከአስመጭነት ጋር ተያይዞ የጉምሩክ፣ የባንክ ፒኤል ሲ የመክፈትና የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ አሰጣጥ ተሟልተው መውረድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በአኩሪ አተር ምርት ላኪነትና በድንጋይ ወፍጮ አስመጭነት የተሰማሩት አቶ ብርሃኑ ገበየሁ በበኩላቸው የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት ወደክልላችን ወርዶ መሰጠት መጀመሩ ለትራንስፖርት፣ ለምግብ፣ ለአልጋና ለሌሎች የምናወጣውን ወጪ እንድንቀንስ ያግዛል ብለዋል ። ውጣ ውረድ መቀነሱ ከመደበኛ ስራችን ሳንርቅ እቅዳችንን በአግባቡ ለማከናወን ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል ። በአማራ ክልል በብዛት የሚመረቱ የጥራጥሬ ምርቶች በቀጥታ ለውጭ ገበያ መላክ እንዲቻል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ባህርዳር ላይ ፅህፈት ቤት እንዲከፍትም ባለሀብቶቹ ጠይቀዋል ። መንግስት ለግሉ ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና መደገፍ ካልቻለ ፈጣን ዕድገት ማምጣት እንደማይቻል የገለጹት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ናቸው። የንግድ ፈቃድና እድሳት አገልግሎት ከማዕከል ወደ ክልል እንዲወርድ መደረጉም ነጋዴው በአካባቢው ሳይንገላታ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል ። ከዚሁ ጋር የሚያያዙ የሙያ ፈቃድና ዕድሳት፣ የምርት ጥራት ቁጥጥር፣ የብሄራዊ ባንክ ፒኤል ሲ፣ የገበያ ዋጋ መረጃና ሌሎች አገልግሎቶች ወደታች እንዲወርዱም ቢሮው እየሰራ መሆኑንን ጠቅሰዋል። በክልሉ ከሐምሌ ከሃምሌ ወር 2011 ዓ.ም  ጀምሮ በተደረገ እንቅስቃሴም በተለያየ ዘርፍ ለተሰማሩ 48 አዲስ አስመጭዎችና ላኪዎች ፈቃድ መስጠቱን አቶ ተዋቸው ተናግረዋል ። የ36 ነባር አስመጪና ላኪዎች እድሳትም ተከናውነዋል ። የፌዴራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር ወይዘሪት አመለወርቅ ሙኔ በበኩላቸው በፌደራል ደረጃ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የአስመጪነት ፈቃድና እድሳት አገልግሎት የተደራሽነት ጥያቄን ለመመለስ ወደክልሎች እንዲወርድ መደረጉን አስረድተዋል። የአስመጪና ላኪዎች የፈቃድ አሰጣጥ ከያዝነው በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እንዲወርድ የተደረገው በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ሲሆን የእነዚህን ተሞክሮ በማየትም በቀጣይ ወደሌሎች ክልሎች እንዲወርድ ይደረጋል። በቀጣይም የባንክ ፒኤል ሲ፣ የጉምሩክና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችም አብረው እንዲወርዱ የአደረጃጀት ስራዎች እንዲሟሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግፊት እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። በውይይት መድረኩ ላይ ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የመጡ አስመጪና ላኪዎች፣ ከፌዴራል ንግድ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። አስመጭና ላኪዎቹ በቀጣይ በተደራጀ አግባብ ችግሮቻቸውን ለመፍታትና የተሻለ  ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችላቸውን  ማህበር መስርተዋል። በክልሉ ፈቃድ አውጥተው በተለያየ ዘርፎች የተሰማሩ 2 ሺህ 615 አስመጪና ላኪዎች እንዳሉም መረጃዎች ያመላክታሉ ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም