ቀጥታ፡

በየካ ክፍለ ከተማ 236 ሔክታር መሬት የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራ ተከናወነ።

አዲስ አበባ ሰኔ7/2010 በየካ ክፍለ ከተማ አንቆርጫ ቀበሌ 236 ሔክታር መሬት የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራ ተከናወነ፡፡ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ  ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከየካ አንቆርጫ ቀበሌ ከፍተኛ እና ተራራማ ቦታዎች ላይ የአፈር፣ የውኃና የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እያከናወነ ይገኛል። በዘንድሮው ዓመትም በየካ አንቆርጫ ቀበሌ በላይኛው ዳንሴ ተፋሰስ 236 ሔክታር መሬት የተራራ ላይ አፈርና የውኃ ጥበቃ ስራ አከናውኗል። በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የአየር ንብረት ለውጥና ተፋሰስ ባለሙያ አቶ አንተነህ ወርቁ እንደሚሉት፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት 236 ሔክታር የተራራ ላይ መሬት የአካባቢና የአፈር ጥበቃ ስራ ተከናውኗል። በየካ የላይኛው ዳንሴ ተፋሰስ ልማት በሚሸፍነው ቦታ ላይ እስከ 2012ዓ.ም ባለው ጊዜ 730 ሔክታር መሬት የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራዎች በቀጣይነት ይከናወናሉ ያሉት አቶ አንተነህ፤ ባለፈው ዓመት  258 ሔክታር መሬት በተፋሰስ ስራ መልማቱን ገልጸዋል። ከፍተኛ ተዳፋት ባለባቸው ቦታዎች ላይ የተራራ ላይ እርከን ግንባታ፣ የድንጋይ እርከኖች ስራ፣ የክትር ስራዎች፣ የጠረጴዛ እርከን፣ የውኃ ማስረጊያና  የጎርፍ ፍጥነት መግቻ ጉድጓዶችን በመስራት ነው የአካባቢ ጥበቃ ስራው እየተከናወነ የሚገኘው። በተራራው ላይ የሚደረገው የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራ የተዳፋቱን ደረጃ በመቀነስ በታችኛው መፋሰሻ ቀበና ወንዝ አካባቢ የሚፈጠረውን የጎርፍ ስጋት በጉልሕ የሚቀንስ መሆኑን ነው አቶ አንተነህ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ እየተከናወነ ያለው የክትርና እርከን ስራ የጎርፍ ፍጥነትን በመቀነስ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጠራቀምና አቅሙ እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው ብለዋል አቶ አንተነህ። ይህ ስራ በቀበና ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የጎርፍ ስጋታቸው እንዲቀንስና በጋራው ላይ በአካባቢ አየር ንብረት መለወጥ ምክንያት የጠፉ ብዝኃ ሕይወት መልሰው እንዲጎለብቱ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል። ባለሙያው አቶ አንተነህ ግርማ  አካባቢው ለጎርፍ የተጋለጠና አፈሩ በቀላሉ የሚሸረሸር መሆኑ በጥናትና በምልከታ ተረጋግጦ የአካባቢ ጥበቃ እየተከናወነበት እንዳለም ይናገራሉ። ከዚሁ በተጨማሪም አፈሩ ሸክላማ በመሆኑ በጎርፍ የመጠረግና የመታጠብ ባሕሪው እንዲቀንስ እየተከናወነ ያለው የአፈርና የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለአርሶ አደሩ፣ ለነዋሪው ሕብረተሰብና ለስነ ምኅዳሩ ጉልሕ ሚና አለው ይላሉ። ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ባሁኑ ሰዓት ከላይኛው ዳንሴ ተፋሰስ በተጨማሪ በላይኛው የካ አካኮ ተፋሰስ 716 ሔክታር ተራራ ላይ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራ እያከናወነ ነው። አሁን ስራው እየተከናወነ ካለበት የካ ክፍለ ከተማ ተራራ ላይ ወደ ፊት የእንጦጦ ከፍተኛ ቦታዎችንና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ተራራ ላይ ድረስ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑም አቶ አንተነህ ተናግረዋል። ከፍተኛ የጎርፍ ፍሰትና የአፈር እጥበት ያለባቸው ቦታዎች ላይ የጋቢዮን ክትር (በሽቦና በድንጋይ የሚታሰር) እርከን ከታች ያለውን የጎርፍ መጠንና ተጋላጭነት ይቀንሳል ሲሉ ያብራሩት ደግሞ የእርከንና የክትር ባለሙያው አቶ መሰለ መኮንን ናቸው። ከ 2 ሺ 800 እስከ 3 ሺ ሜትር ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ ያለው የየካ ተራራ  ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኝ መሆኑን ተከትሎ ለጎርፍ ተጋላጭነቱ ከፍ ያለ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም