ቀጥታ፡

በቋራ ወረዳ ጎርፍ በ14 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የነበረ ቡቃያ አወደመ

ጎንደር ኢዜአ ጳጉሜ 1/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ትናንት የጣለው ከባድ ዝናብ በ14 ሺህ ሄክታር መሬት ቡቃያ ላይ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ወንድይፍራው ሙሉየ እንደገለፁትአደጋው የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ ባጋጠማቸው በወረዳው በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች ላይ ነው። በአደጋው ከ11 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በሰሊጥ ሰብል በተሸፈነ ማሳ ላይጉዳት የደረሰ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በማሽላ፣ በአኩሪ አተር፣ በጥጥ፣ ማሾ፣ በርበሬና ሌሎች ሰብሎች መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል ። ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው በዚሁ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በወረዳው የሚኖሩ 3 ሺህ 900 አርሶ አደሮችን ለችግር እንዲጋለጡ አድርጎአቸዋል ። ከሰብሉ በተጨማሪ 27 የመኖሪያ ቤቶች ያወደመ ሲሆን በሰውና በእንስሳት ህይወት ላይ ግን ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም ብለዋል ። የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤትተጎጂ አርሶ አደሮች ማሳቸውን ቶሎ በሚደርሱ ሰብሎች እንደገና እንዲሸፍኑ አስፈላጊውን የዘርና የባለሙያ እርዳታ እንደሚያደርግላቸው አቶ ወንድይፍራው ገልፀዋል ፡፡ በወረዳው አየር ንብረት መሰረት የጤፍ ሰብል ከዚህ በኋላ ተዘርቶ ምርት መስጠት የሚችል በመሆኑ ትኩረት እንደሚሰጠው የገለፁት ኃላፊው የወደመውን ሰብል ለማካካስ በተለይ መስኖ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል ። በሰብሎቻቸው ላይ ጉዳት ከደረሰባቸው አርሶ አደሮች መካከል የምርት ገለጉ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መልካሙ ደስታው በሰጡት አስተያየት አራት ሄክተር የሰሊጥ፣ ሁለት ሄክታር የማሽላና 1 ሄክታር የአኩሪ አተር ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ ወድሞባቸዋል፡፡ ቡቃያው በጥሩ ቁመና ላይ ስለነበረ በጎርፍ አደጋው ከ150 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል፡፡ የማር ውኃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቸኮል ቀናው በበኩላቸው በደህና ሁኔታ ላይ የነበረ ስድስት ሄክታር ሰሊጥ፣ ሁለት ሄክታር ጥጥና ሁለት ሄክታር ማሽላ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ተናግረዋል ። በአደጋው 200 ሺህ ብር የሚገመት ሃብት እንዳጡ አርሶ አደሩ ገልፀው የጠፋውን ሰብል ለማካካስ የመንግስት እገዛ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም