ቀጥታ፡

በከተማዋ የሚገኙ 1ኛ ደረጃ እና አፀደ ህፃናት የግል ትምህርት ቤቶች የቅድመ ዝግጅት ስራ እያጠናቀቁ ነው

ጳጉሜ 1/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የ1ኛ ደረጃ እና የአፀደ ህፃናት የግል ትምህርት ቤቶችን ለመጭው ትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል።

የኢዜአ ሪፖርተር በከተማዋ የሚገኙ አንድ አንድ የግል ትምህርት ቤቶች ባደረገው ቅኝት ለ2012 የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑን ተልክቷል።

ከቅድመ ዝግጅት ስራዎች መካከልም የተማሪዎች ምዝገባና የመማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የትምህርት ቤቶችን ግቢ የማጠር እና የመምህራን ቅጥር ማሟላት የሚሉት በዋናነት ይገኙበታል።

የፊቸር ጀኔሬሽን ሆፕ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፀጋየ ተፈራ እንደገለፁት ከሃምሌ 2/2011 ጀምሮ በትምህርት ቤቱ እየተካሄደ ባለው የቅድም ዝግጅት ሥራ ከምዝገባ ጎን ለጎንም የመማሪያ ክፍሎችን የማስተካከልና ያልተሟሉ ግብዓቶችን በማሟላት ምቹ የመማር ማስተማር ከካባቢን ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ሰዓትም የመማሪያ መጽሀፍትን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በማምጣት ለተማሪዎች እያከፋፈሉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጸጋዬ፤ መምህራን አመታዊ እቅዳቸውን እና የመለማመጃ ጥያቄዎችን በማዕከል ደረጃ በጋራ አዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎች የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥማቸው ከወላጆች ጋር በመሆን ከትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅትች ጋር በመወያየት መስማማታቸውንም ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ አስፓልት ዳር በመሆኑ አደጋ እንዳያጋጥም ከአካባቢው ፖሊስ ጋር በቅንጅት ለመሰራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውንና  የተማሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅም የተሟላ የጥበቃ አገልግሎት መሟላቱም ተገልጿል።

በመገባደድ ላይ ባለው የክረምት ወቅት ከመንግስተ ጋር በመናበብ የአገሪቱ የትምህርት ስርኣት በሚፈቅደው መሰረት የትምህርት ግብዓትን በማሟላትና ምቹ የመማር ማስተማር ስርዓትን ለመፍጠር ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የሮሆቦት ቪዥን አካዳሚ የ1ኛ ደረጃና የአፀደ ህፃናት ትምህርት ቤት ባለቤት  ወይዘሮ ዘይቱና ሁሴን ናቸው።

ወይዘሮ ዘይቱና እንዳሉት በቅድመ ዝግጅቱ የሀገሪቱን የትምህርት ስርዓት ባማከለ መልኩ የአጸደ ህፃናት ተማሪዎች አካባቢያቸውን በደንብ እንዲገነዘቡ የሚያስችልና እድሜያቸውን የሚመጥኑ መፃሃፍት እየተዘጋጀ ነው።

ልጃቸው በእረፍት ጊዜው የተለያዩ መፅሃፍትን በማንበብ ለመጭው የትምህርት ዘመን መዘጋጀቱን የተናገሩት በሮሆቦት የአፀደ ህፃናትና የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያገኘናቸው ወይዘሮ አመለ ድረስ፤ ከትምህርት ቤቱ ጋር በመነጋገርም ለልጃቸው ማሟላት ያለባቸውን እያሟሉ ነው።

በፊውቸር ጀኔሬሽን ሆፕ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጃቸውን ስያስመዘግቡ ያገኘናቸው ሌላው ወላጅ አቶ ያሬድ ሁነኛው፤ ለልጃቸው የሚያስፈልገውን የትምህርት መርጃ መሳሪያ ማሟላታቸውን ተናግረው፤ ትምህርት ቤቱም ከግቢ ንጽህና ጀምሮ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሪጉላቶሪ ኤጀንሲ በበኩሉ ለ2012 የትምህርት ዘመን ምቹ የመማር መስተማር እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በኤጀንሲው የትምህርት ስልጠና ጥራት የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ  ዋና ዳይይሬክተር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ለኢዜአ እንደገለጹት በግል ትምህርት ቤቶቹ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ባለሃብቶቹ የቅድመ ዝግጅት ስራ እንዲሰሩ ተደርጓል።

ትምህርት ቤቶቹ መንግስት ባስቀመጠው የትምህርት ስርዓት መሰረት የማስተማር ሥራን እንዲጀምሩ አቅጣጫ መሰጠቱን የተናገሩት  ዋና ዳይሬክተሯ፤ በከተማ ደረጃ በ2011 ትምህርት ቤቶቹ ከግብዓት፣ ከሂደትና ከውጤት አንፃር የነበራቸው አቋም ተመዝኖ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡት መሸለማቸውን ገልጸዋል።

በአንጻሩም የምዘና መስፈርቱን ያላሟሉና እንዲያስተካክሉ ተነግሯቸው ማስተካከል ያልቻሉ 29 የመጀመሪያ ደረጃ እና 24 የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 569 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና 919 መዋዕለ ህጻናት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሪጉላቶሪ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም