ቀጥታ፡

ማምሻም ዕድሜ ነው

ጳጉሜ 1/2011  የ80 ዓመቷ የዕድሜ ባለጸጋ አዲሱ ዓመት ከዚህ ቀደም ካለፉት ዓመታት በተለየ የመኖር ጉጉት ፈጥሮባቸዋል። ዕድሜያቸው በትክክል ባያውቁትም ከ80ዎቹ እንደሚዘል ግን እርግጠኛ ናቸው። ዛሬ ላይ የዕድሜያቸውን ግማሽ በኖሩበት ቤት የአልጋ ቁራኛ ሆነው ይገኛሉ። ከአብራካቸው የተከፈሉ ሶስት ልጆች ቢኖሩም ከእርሳቸው ጋር የምትኖረው የበኩር ልጃቸው ወይዘሮ ብርቱካን በየነ ናት። ወይዘሮ ጸሃይነሽ እንየው በጉለሌ አካባቢ ጠላ በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ከንጋት እስከ ምሽት እረፍት አልባ ኑሮ እንዳሳለፉ የበኩር ልጃቸው ታስታውሳለች። የኑሮ ጫናው እየከበደ ለልጆቻቸው የዕለት ጉርስ እንኳን ማቅረብ ሲያቅታቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጃቸው ከቤት ወጥተው በዚያው ይቀራሉ። ወይዘሮ ብርቱካን እዛው ተወልዳ ባደገችበት የእናቷ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሶስት ልጆችን አፍርታ እሷም እንደ እናቷ ያለ ትዳር አጋር ልጆቿን በችግር እያሳደገች ትገኛለች። በዚህች ጠባብ ቤት ውስጥ አዛውንቷ ወይዘሮ ጸሃይነሽን ከሶስት የልጅ ልጆች እንዲሁም ለረጅም ዓመታት ከእነርሱ ጋር ከኖረች ሌላ ሴት ጋር በጋራ ይኖራሉ። በድምሩ ስድስት ሰዎችን ተዓምር በሚመስል ሁኔታ የምታኖረው ይህች ጠባብ ቤት 'ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል' እንዲሉ ማብሰያም ሆነ መጸዳጃ ቤት የሌላት በመሆኑ ኑሯቸውን የበለጠ ከባድ እንዳደረገው ወይዘሮ ብርቱካን ትገልጻለች። በዚህ ሁኔታ ጊዜ ጊዜን እየወለደ ዓመታት ተቆጠሩ። ወይዘሮ ጸሃይነሽም እርጅና እየተጫጫናቸው ጉልበታቸው እየደከመ ነገ አዲስ ቀን እንደሚሆን ተስፋ እያደረጉ ኑሮና አዳራቸውን አልጋ ላይ ካደረጉ ሰነባበቱ። ባለፈው ዓመት በከተማዋ የአቅመ ደካሞችንና የአረጋውያንን ያረጀ ቤት የማደስና የመስራት የበጎ ስራ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በርካታ የበጎ ፍቃድ አገልጋይ ወጣቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጭምር ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንን ቤት የማደሱን ተግባር አጠናክረው ቀጥለዋል። ወይዘሮ ጸሃይነሽ በሚኖሩበት አካባቢ የእርሳቸውን ያህል የተጎሳቆለና የተጎዳ ቤት ባለመኖሩ የወረዳው የበጎ ፍቃድ አስተባባሪዎች የመጀመሪያ ስራቸውን የእርሳቸውን ቤት ማደስ አድርገዋል። 'ማምሻም ዕድሜ ነው' እንዲሉ ምንም እንኳን አዛውንቷ እርጅና ቢጫናቸውና ከአልጋ መነሳት ባይችሉም በዕድሜያቸው መደምደሚያ የመኖር ተስፋቸውን ሊያለመልም የሚችል አጋጣሚ በማግኘታቸው በለሆሳስም ቢሆን ቤታቸውን ላደሱላቸው በጎ ፈቃደኞች ምስጋና ከማቅረብ አልተቆጠቡም። አዲስ ዓመት አዲስ ህይወት አዲስ ተስፋና የመኖር ጉጉትን ይዞ እንደመምጣቱ የአዛውንቷ የበኩር ልጅም የቤታቸው መታደስን ተከትሎ በመጪው አዲስ ዓመት የራሷንና የቤተሰቧን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ ጉጉት እንዳላት አስታውቃለች ። አቶ ዓለምሰገድ መክብብ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ነው። ''በበጎ ፈቃድ ተግባር መሰማራት ከምንም በላይ የሚሰጠው የመንፈስ እርካታን ነው'' ይላል። የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ከስሟ ውጪ ግብሯ አሮጌ መገለጫዋም በየመንገዱ የሚጣል ቆሻሻ፣ ያረጁና የወዳደቁ ጎጆዎች እንዲሁም ፕላን አልባ ግንባታዎች ሆነው ቆይተዋል። ይህችን ከተማ ስሟንና ሃላፊነቷን በሚመጥን መልኩ ግንባታዋን ለማከናወንና ጽዳቷን ለመጠበቅ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ግልጽ ነው። ይሁንና አሁንም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የተጎሳቁሉና የፈራረሱ ጎጆዎች ብሎም በላስቲክና በካርቶን የተወጠሩ ማደሪያዎችን  ማየት የተለመደ ሆኗል። እነዚህ ጎጆዎች ናቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ለጊዜውም ቢሆን በተሻለ ሁኔታ ዕድሳትና ጥገና የሚደረግባቸው። አዛውንቶቹም ከብርድና ንፋስ ከፀሐይና ዝናብ እረፍት የሰጣቸውን ፈጣሪ እያመሰገኑ በተሻለ ቤትና በአዲስ የመኖር ተስፋ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሚዘጋጁት። ለወይዘሮ ጸሃይነሽም በዕድሜያቸው ካሳለፉት አዲስ ዓመት በተለየ የዘንድሮው ከፍተኛ የመኖር ጉጉት የፈጠረላቸው ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም