የሸማቾች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በበቂ መጠንና ተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርቡ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የሸማቾች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በበቂ መጠንና ተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርቡ ተገለፀ
አዲሰ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 1/2011 በበዓል ምክንያት የሚፈጠረውን የገበያ አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በቂ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን በተጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ገለጸ። ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ የፈሳሽ ዘይት ለሸማቾች በድጎማ ለማቅረብ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት አስታውቋል። የመዲናዋ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮና ህብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ የአዲስ ዓመት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትና ስርጭትን በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ እንዳሉት፤ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ለሸማቹ በቂ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ። በተለይም በጤፍ ምርት ላይ የነበረውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጣልቃ በመግባት ''ከዚህም በላይ እንዳያሻቅብ ማረጋጋት ችለናል'' ብለዋል። አዲሱን የ2012 ዓመት ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ኤጀንሲው ከአማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ጋር በመተባበር ለሸማቹ አስፈላጊ ግብዓቶችን እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ የቁም እንስሳት አርቢዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በጎችን በማስገባት ከ2 ሺህ 300 ብር ባልበለጠ ዋጋ እናቀርባለን ብለዋል። ፈሳሽ ዘይት ባለአምስት ሊትር በ365 ብር፣ አይብ ከ60 እስከ 65 ብር፣ እንቁላል ከ3 ብር 70 ሳንቲም እስከ 3 ብር 85 ሳንቲም ብር ጤፍ ከ 2 ሺህ 400 እስከ 2 ሺህ 800 ብር ዋጋ እናቀርባለን ብለዋል። በከተማዋ ባሉ ከ 220 በላይ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች አንድ ኪሎ ስጋ ከ170 ብር ባልበለጠ ዋጋ እንደሚሸጥ ገልጸዋል። በጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ፣ ነጭና ቀይ ሽንኩርት፣ ቅቤ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ስኳርና ሌሎችም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች እንደሚቀርብ ገልጸዋል። ''የመዲናዋ ሸማቾች የሚፈልጓቸው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚቀርቡ ሸማቾች ሃሳብ አይግባችሁ'' ብለዋል። ''ኤጀንሲው በቂ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብም ባለፈ ገበያውን በማረጋጋት ሰላማዊና ፍትሃዊ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል'' ዋና ዳይሬክተሩ። ቀጣይነት ያለው ፍትሃዊ የንግድ ውድድር ሥርዓት ለመገንባት ከደቡብ አፍሪካና አሜሪካ ልምድ ወስደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስታዊ አቅንምን ማጎልበት፣ የነጋዴውን አመለካከት መቀየርና የገበያውን መሰረተ ልማት ማስፋፋት የትኩረት መስኮች መሆናቸውንም ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ለአዲሱ ዓመት ፍጆታ የሚውል 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ 120 ሺህ ኩንታል ስኳርና 165 ሺህ ኩንታል ስንዴ ዱቄት የሚቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል። በመዲናዋ የሚከሰተውን የዋጋ ግሽበት በዘላቂነት ለመፍታት ከቅንጅት ባለፈ የቁጥጥር አሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋም ተናግረዋል። ''በመደበኛው የንግድ ስርዓት ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትን ተከታትለን እርምጃ እንወስዳለን'' ብለዋል። ከአሁን ቀደም በ5 ሺህ 300 የንግድ ማዕከላት ላይ ቁጥጥር ተደርጎ 91 ወፍጮ ቤቶች፣ 56 አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ማዕከላት፣ 63 ስጋ ቤቶች ከአገልግሎት መታገዳቸውን ገልጸዋል። ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ የፈሳሽ ዘይት ለሸማቾች በድጎማ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንቅስቃሴ መጀመሩንም ቢሮው አስታውቋል።