በ19ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ እየተመራን ኢትዮጵያን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኑሪ ማለት ምኞት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ እየተመራን ኢትዮጵያን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኑሪ ማለት ምኞት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ
አዲሰ አበባ ኢዜአ ጳጉሜ 1/2011 ''በግልም በቡድንም በ19ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ እየተመራን ኢትዮጵያን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኑሪ ማለት ምኞት ነው'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። እያንዳንዱ ዜጋ እርስ በርስ ከሚያጋጭ ጎታች አስተሳሳብ ወጥቶ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ሃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል። በቻይና የትምህርት እድል ያገኙ 228 ኢትዮጵያውያን ትናንት በብሄራዊ ቤተ-መንግስት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። እድሉን ካገኙት ኢትዮጵያውያን መካከል 66 የሚሆኑት በሶስተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ናቸው። ይህም ቻይና በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ለታዳጊ አገሮች ለመስጠት ከወጠነችው ነጻ የትምህርት እድል ውስጥ ኢትዮጵያ 16 ነጥብ 5 ድርሻ በመያዝ ቀዳሚ የእድሉ ተጠቃሚ አገር ሆናለች። ከዚህ በተጨማሪ በዓመቱ ከ800 ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በቻይና የአጭር ጊዜ ስልጠና እንደተሰጣቸው ተገልጿል። የትምህርት እድሉ የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም አንዱ አካል ሲሆን፤ ከሰው ሃብት ልማት ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትብብርን ማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ወቅት "ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ካሰብን በ19ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ከመባላት ወጥተን ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን መሻገር አለብን" ብለዋል። ይህን ማድረግ ካልቻልን የኢትዮጵያ እድገት ህልም ይሆናል ነው ያሉት። ለዚህም መፍትሄው ትምህርት እንደሆነ አስገንዝበዋል። የቻይና እድገት ከመከፋፋል ወጥቶ በትብብር መቆም ያለውን ጥቅም እንደሚያሳይ በመጠቆም። ሰልጣኞች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ችግር የሚፈታ ቁልፍ ትምህርት መሆኑን ተገንዝበው በቆይታቸው የተሻለ እውቀት ለመቅሰም ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። "ከሚሰጣችሁ ቀጥተኛ ስልጠና በተጨማሪም ለአገራችሁ የሚጠቅም ማናቸውንም ዓይነት ልምድ ቀስማችሁ መምጣት አለባችሁ" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መክረዋል። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጄን በበኩላቸው ታዳጊ አገሮች ያላቸው ትልቁ አቅም የሰው ሃብት እንደሆነ አውስተዋል። የእስያ አገሮች የእድገት ምስጢር የሰው ሃብት ልማት መሆኑን ያብራሩት አምባሳደሩ፤ "በሰው ሃብት ልማት ላይ የሚፈስ መዋለ ንዋይ ከኢንቨስትመንቶች ሁሉ ትልቁ ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ያደረጉትን የመጀመሪያ ንግግር በማስታወስ። አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከሰው ሃብት ልማት በተጨማሪ በሌሎች መስኮች ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል። ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋጋራቸው የነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ጠንክረው በመማር አገራቸውን እንዲያገለግሉ ያስተላላፉትን ማሳሳቢያ ለመተግበር የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ቻይና እ.አ.አ እስከ 2018 መጨረሻ ድረስ ከ7 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል የሰጠች ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከ680 በላይ የሚሆኑት ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ የሰለጠኑ ናቸው።