የአገር እድገት አካባቢን በሚሻገር የአእምሮ ልማት እንጂ ዜጋን በሚከፋፍል ጎታች አስተሳሰብ አይገነባም-ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የአገር እድገት አካባቢን በሚሻገር የአእምሮ ልማት እንጂ ዜጋን በሚከፋፍል ጎታች አስተሳሰብ አይገነባም-ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 30/2011 የአገር እድገት አካባቢን በሚሻገር የአእምሮ ልማት እንጂ ዜጋን በሚከፋፍል ጎታች አስተሳሰብ አይገነባም ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በቻይና የትምህርት እድል ያገኙ ኢትዮጵያውያንን በብሄራዊ ቤተመንግስት በተሰናዳ የአሸኛኘት ስነ-ስርዓት ላይ ነው። የትምህርት እድሉ የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም አንዱ አካል ሲሆን፤ ከሰው ሃብት ልማት ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትብብርን ማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል። በትምህርት እድሉ 228 ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ሆነዋል። ከእነዚህም ውስጥ 66 የሚሆኑት በሶስተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ናቸው። ይህም ቻይና በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ለታዳጊ አገራት እሰጠዋለሁ ብላ ከወጠነችው ነጻ የትምህርት እድል ውስጥ ኢትዮጵያ 16 ነጥብ 5 ድረሻ በመያዝ ቀዳሚ የእድሉ ተጠቃሚ አገር አድርጓታል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ እድገት በፍጥነት እንዲረጋገጥ ቁልፉ መሰረት የሰው ልማት መሆኑን መንግስታቸው እንደሚገነዘብ አስረድተዋል። መንግስት በውጭ አገራት ከሚያመቻቻቸው ነፃ ስልጠናዎች በተጨማሪ በአገር ውስጥም ብቁ ዜጋ ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራም ጨምረው ገልፀዋል። "አገር የሚገነባው አካባቢን በሚሻገር የአእምሮ ልማት እንጂ በከፋፋይ አስተሳሳብ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሰልጣኞች ይህን በመገንዘብ በቆይታቸው የተሻለ እውቀት ለመቅሰም እንዲጥሩ አሳሳስበዋል። "ከሚሰጣችሁ ቀጥተኛ ስልጠና በተጨማሪም ለአገራችሁ የሚጠቅም ማናቸውንም ዓይነት ልምድ ቀስማችሁ መምጣት አለባችሁ" ሲሉም መክረዋል። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጄን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከሰው ሃብት ልማት በተጨማሪ በሌሎች መስኮች ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አውስተዋል። ቻይና እንደ አውሮጳውያን አቆጣጣር እስከ 2018 መጨረሻ ድረስ ከ7 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል የሰጠች ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከ680 በላይ የሚሆኑት ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ የሰለጠኑ ናቸው።