ሁለተኛው የቢዝነስ ሩጫ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው የቢዝነስ ሩጫ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 ሁለተኛው የቢዝነስ የሩጫ ውድድር እሁድ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ይህን ሩጫ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። ይህ የሩጫ ውድድር ''ለኢንዱስትሪ ልማት እንሩጥ'' በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ አዘዘው እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአገልግሎት ዘርፍ እንጂ በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው። የውድድሩ ዓላማም በአገሪቷ የሚገኙ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ መልእክቶችን ማስተላለፍ መሆኑን ጠቅሰዋል። ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሰማሩ ለትውልዱ የሚተርፍ ትልቅ እሴት እንደሚጨምሩ በመገንዘብ "በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል" ያሉት ኢንጂነር መላኩ፤ ብዙዎች የሚሰሩት በአገልግሎት ዘርፍ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል። በዕለቱ በተሳታፊዎች የ400 ሜትርና በአትሌቶች የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ ይከናወናል። በዚህ ሩጫ ላይ ባለሀብቶችና ሠራተኞቻቸው፣ አርቲስቶችና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚሳተፉበትም ተነግሯል።