ነገ ጳጉሜ 1 ቀን በሚካሄደው አገር አቀፍ ጸሎተ ምህላ ስነ-ስርዓት ላይ መላው ህዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ነገ ጳጉሜ 1 ቀን በሚካሄደው አገር አቀፍ ጸሎተ ምህላ ስነ-ስርዓት ላይ መላው ህዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ
ነሀሴ 30/2011 ነገ ጳጉሜ 1 ቀን 2011 በኢትዮጵያ ሁሉም ቤተ እምነቶች በሚካሄደው አገር አቀፍ ጸሎተ ምህላ ስነ-ስርዓት ላይ መላው ህዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ። በመላው ኢትዮጵያ ነገ ጳጉሜ 1 ቀን 2011 አገራዊ የፀሎትና ምህላ ቀን እንዲሆን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ማወጁ የሚታወስ ነው። የፀሎትና ምህላ ማወጁ ዓላማ መላው ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ዓመት በአዲስ አስተሳስብ በመቀበል የተከሰቱ አገራዊ ግጭቶች ተፈትተው ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ እንዲሰፍን መላው ዜጋ በየእምነቱ ፈጣሪውን እንዲማፀን ማድረግ መሆኑን ጉባኤው አመልክቷል። የፀሎተ ምህላውን ስነ-ስርዓት በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ሃይማኖታዊ መርሃ ግብሩ ለአገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለአገር ብልፅግና የጎላ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም በየቤተ እምነቱ እንዲሳተፍ አሳስበዋል። ባለፈው ዓመት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶችና እርሱንም ተከትሎ የተስተዋሉት ማህበራዊና ሰብአዊ ጉዳቶችን ለማከም ሁሉም በፀሎት መትጋት እንዳለበትም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ችግሮች ተፈትተው መጪው ዘመን የደስታና ተድላ እንዲሆን ሁሉም ወደፈጣሪው እንዲማፀን አሳስበዋል። አክለውም የፀሎትና ምህላ ስነ-ስርዓቱ ላይ አረጋዊያን፣ ወጣትና ህጻን ተብሎ ሳይለይ ሁሉም በመካከሉ ያለውን ልዩነት በማስታረቅ በአንድ መንፈስ ቆሞ በየእምነት ተቋማቱ፣ በሥራ ቦታውና በሚመቸው መንገድ ሁሉ አምላኩን በማስታወስ ለአገር ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና ይፀልይ ዘንድ ኃላፊነት አለበት ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። የጸሎትና ምህላ አዋጁ ዓላማ ይሰምር ዘንድ ህዝቡ፣ የፌዴራልና ክልል መንግስታት ባለስልጣናት፣ የጸጥታ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ እናቶች፣ ወጣቶችና የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቅርበዋል።