የትምህርት ተቋማት በሰላም ጉዳይ ላይ ለመስራት ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ተቋማት በሰላም ጉዳይ ላይ ለመስራት ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አለባቸው
ነሐሴ 30/2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በሰላም ጉዳይ ላይ ለመስራት ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ። ኤች.ደብሊው.ፒ. ኤል የተሰኘው የኩሪያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የዓለም ሃይማኖቶች ህብረት ጉባኤን ለአምስተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል። ዛሬ ከቀትር በኋላ በተካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ መንግስታዊ ተቋማትንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የወከሉ ግለሰቦች ታድመዋል። የአዲስ አበባ ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩትን ወክለው ንግግር ያደረጉት ዶክተር ፋሲል ንጉስ በሰላም ጉዳይ ላይ አትኩሮ ከሚንቀሳቀሰው 'ኤች.ደብሊው.ፒ.ኤል' የተሰኘው ኩሪያ በቀል ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። ሰላምን ማረጋገጥና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ በተለይም በለውጥ ሂደት ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳይ ነው ሲሉ ዶክተር ፋሲል ገልፀዋል። ስለሆነም እንደሰላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል በሰላም ጉዳዮች ከሚያተኩሩ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለመስራትና ኃላፊነቱን ለመወጣት ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚያከናውንም አረጋግጠዋል። የ'ኤች.ደብሊው.ፒ.ኤል' የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ዩ ጃን ጄ በበኩላቸው ድርጅታቸው በሌሎች አገራት እንደሚያደርገው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥም ከተለያዩ የሃይማኖት፣ የትምህርትና የሙያ ማህበራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ወደፊትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የወጣት አደረጃጅቶች ጋር በቅርበት እንሰራለን ብለዋል። 'የለም ኢትዮጵያ አካባቢ ልማት ማኅበር'ን ወክለው የተገኙት አቶ ሞገስ ወርቁ ቀውስ በበዛባት ዓለም በተለይም በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ሰላም መቅደም አለበት በማለት ተናግረዋል። በሰላም እጦት ምክንያት 60 ሚሊዮን ዜጎች በዓለም ላይ መፈናቀላቸውን፣ ከ260 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ግብዓት ማጣታቸውን፣ ትምህርታቸውንም ማቋረጣቸውን ገልፀዋል። በተለይም ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመቅርፍ የዕውቀት ምንጭ የሆኑ ትምህርት ተቋማት፣ በሰላም ባህል ጉዳይ ከሌሎች ተቋማት ጋር ተግባራዊ ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሰላም ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግስት ያሉትን ሁሉ ድርሻ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ወላጆች ለልጆቻቸው፣ የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው፣ ትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው ስለሰላም ማስተማር ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል። መንግስትም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበትም ሲሉ አስገነዝበዋል። የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲም ትምህርት ለነገ አገር ተረካቢ ትውልድ መሰረት የሚጥል መሳሪያ እንደሆነ ገልጸው፤ የትምህርት መሳሪያ ለማቅረብም ሆነ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ግን ሰላምን ማስፈን እንደሚያሻ አብራርተዋል ተማሪዎችን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መምራት የሚቻለው ሰላም ሲረጋገጥ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ዩሃንስ "ሰላምን በቤታችን፣ በትምህርት ቤታችንና በአገራችን ለማስፈን በጋራ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። ማህበሩም የሰላም መልክተኛ ከሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም እንደሚሰራ ገልጸዋል። የዓለም የሰላም ምክር ቤት አባል የሆኑት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና በበኩላቸው የትምህርት ተቋማት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሰለስላም ማስፈንና ጦርነትን ማስቆም ጉዳዮች ላይ በትብብር ሊመክሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። 'እንደከፍተኛ ትምህርት ተቋም አመራር ከሰላም በላይ አጀንዳ የለኝም' ያሉት ዶክተር ብርሃነመስቀል፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር ተቋማቸው የሰላም መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል። "ሰላም ስለተፈለገ ብቻ እንደማይመጣ ገልጸው፤ ከውስጥ የሚጀምር ሰላምን በማስፋት ወደህብረተሰቡ ለማስረጽ ከመድረክ ባለፈ ፍሬው እንዲታይ በጋራ መስራት ይጠይቃል" ብለዋል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዚህ ረገድ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸው መቻቻልን በተግባር በማሳየት ለሰላም መስፈን አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።