ቀጥታ፡

በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በችግኝ የመሸፈኑ ስራ ይቀጥላል

ነሐሴ 30/2011 በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በቢሊዮን ችግኝ የመሸፈኑ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ። የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብና ተጨማሪ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ገልፀዋል። የችግኝ ማፍላት ስራው በዚህ ዓመት በተለየ ትኩረት በከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተካሄደ መሆኑንና ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኝ የመትከል ስራውም በስኬት መጠናቀቁን አውስተዋል። ቀደም ሲል ከችግኝ ተከላ ጋር ተያይዞ ይነሳ የነበረውን ባለቤት የማጣትና የክትትል ስራ በማጠናከር የተተከሉት እስኪፀድቁ የሚንከባከብ አካል በየአካባቢው መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት የተተከሉ ችግኞችን ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ማድረግ፣ የደረቁትን በመንቀል በሌላ መተካት፣ ውሃ ማጠጣትና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቀጣይ ለሚተከሉት ችግኞች ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስ። የደቡብ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በበኩላቸው በክልሉ በ2011 ዓ.ም ከ830 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ነው የተናገሩት። ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተተከሉ ችግኞች ከ78 በመቶ በላይ መፅደቃቸውንም ጠቅሰዋል። የነበረውን የመንከባከብ ችግር ለመፍታት የተተከሉትን ችግኞች ለየአካባቢው ማህበረሰብና ተቋማት በመስጠት ውጤታማ መሆን እንደተቻለም አክለዋል። የችግኝ እንክብካቤ በማጠናከር የደን ሽፋንን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። ለቀጣዩ ተከላ ለችግኝ ማፍያ የሚያገለግል ላስቲክና ዘር መዘጋጀቱንና የችግኝ ማፍያ ቦታዎች እየተጠኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 225 ሺህ ሄክታር መሬት በችግኝ ለመሸፈን ከ1 ነጥብ 17 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዟልም ብለዋል አቶ ሳሙኤል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 98 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቦና ያዴሳ ናቸው። በደን ዘርፍ በዓመቱ ጥሩ ስራ መሰራቱን ገልጸው የመንከባከቡም ስራ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግኞቹ በተተከሉባቸው አካባቢዎች የእንክብካቤ ስራው በአግባቡ እንዲካሄድ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል። የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል ግብረ ኃይል መዋቀሩንና በዚህ ተግባር በሚሳተፉ ግለሰቦች ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ ደኑን በባለቤትነት እንዲንከባከብና ከዘርፉም ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 15 ነጥብ 5 በመቶ እንደሆነ ይነገራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም