ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችን ምክንያት በየዓመቱ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ታጣለች

ነሀሴ 30/2011 ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ የ31 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደሚደርስባት አንድ ጥናት አመለከተ። የጤና ሚኒስቴር ከዓለም ጤና ድርጅትና ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችን ላይ ያስጠናውን ጥናት ዛሬ ይፋ ሆኗል። ጥናቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢኮኖሚና በጤና ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ለመከላከልና የቀጣይ 15 ዓመት እቅድ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተጠና ነው። ትኩረቱንም የልብ ህመምና የደም ዝውውር ችግር፣ የካንሰር በሽታ፣ የስኳር ህመምና ከአተነፋፈስ ችግር ጋር የተያያዘ ነው። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2017 የተካሄደው ጥናት የአገሪቱ ዜጎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በአግባቡ ስራ ገበታቸው ላይ አይገኙም፤ በስራቸው ውጤታማ አይደሉም እንዲሁም አገሪቱ ለህክምና 31 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ታወጣለች ይላል። ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ሁለት በመቶውን የሚሽፍን ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከነዚህ በሽታዎች የተነሳ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ40 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለሞት ይዳረጋሉ። ከዚህኛው ጥናት አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በተደረገ ጥናትም በኢትዮጵያ በተለያዩ በሽታዎች ህይወታቸው ከሚያልፉ ሰዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችና በድንገተኛ አደጋዎች ነው ህይወታቸው የሚያልፈው። የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ደረጃ አሳሳቢና በኢኮኖሚው ላይም ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል። በመሆኑም እነዚህን በሽታዎች በዘላቂነት ለመከላከል ለ15 ዓመት የሚቆይ በጥናት ላይ የተመረኩዘ ስትራቴጂክ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህም ያለአግባብ የሚወጣውን ወጪ ለመከላከል፣ ጤናማ ማህበረሰብ ለማፍጠርና አምራች ኃይልን ለማፍራት እንደሆነ ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት። ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ትንባሆ ማጨስ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮልና ጨው መጠቀም፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ በአብዛኛው መንስኤዎች ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ 40 ሚሊዮን አልኮል፣ 16 ሚሊዮን ጫት፣ አራት ሚሊዮን ደግሞ ሲጋራ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ጥናቱ ያመለክታል። ይህ በጤና ላይ የሚያደርሰውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ሚኒስቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚስችል ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ አዋጆችንና ህጎችን በማውጣት እየሰራ ነው ብለዋል። ዕቅዱ በቀጣይ 15 ዓመታት በሚከናወኑት ተግባራት 1 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎችን ከሞት መታደግ የሚያስችል ነው ተብሏል። ቀደም ሲል የሲጋራና የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያን የሚከለክል አዋጅ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ የጨው መጠን አጠቃቀምና ጫትን በተመለከተ አዋጆችንና ህጎችን ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም ማህበረሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ እንዲያደርግ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች መንገዶችን ከተሽከርካሪ ነጻ በማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውሰዋል። ለ15 ዓመታት የሚከናወነውን እቅድም ለማሳካት ከ242 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ገንዘቡ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና ከመንግስት እንደሚገኝ ይገልጻሉ። ከገንዘቡ መካከል 20 ቢሊዮን ብሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚውል ሲሆን ቀሪው ደግሞ ለህክምና ወጪ እንደሚሆን አስታውቀዋል። የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካዮችም ተላላ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም