በኢትዮጵያ ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያስችላል የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያስችላል የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ነሐሴ 30/2011ቨ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዲኖረውና አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ ያግዛል የተባለ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆነ። ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ15 ሚሊዬን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ነው። በዋነኝነት በኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በአማራ ክልሎች 28 ወረዳዎች የሚገኙ የቡና አምራች አርሶ አደሮችን የሚያሳትፈው ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ15 ሚሊዬን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ለፕሮጀክቱ ትግበራ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በዓይነትና በባለሙያ ጭምር ያቀርባል። የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ የፕሮጀክቱን ይፋ መሆን ለማብሰር በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ አቅምን ማጎልበትና አገራዊ ምጣኔ ኃብቱን ማጠናከር የፕሮጀክቱ ግብ ነው። የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻል፣ የቡና በሽታን መከላከል፣ በሽታን የሚቋቋም የቡና ዝርያን ማቅረብና ልማቱን በምርምር መደገፍ በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል መሆናቸውንም አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ የአገሪቱን የቡና ግብይትና ድርድር አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትም በፕሮጀክቱ እንደሚከናወኑ ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል። የቡና አምራቾች የቡና ምርት ላይ እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ በማቅረብ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማገዝም በፕሮጀክቱ የተያዘ ግብ መሆኑን አክለዋል። የመንግስትና የግሉን ዘርፍ አቅም በመገንባት በቡና ልማት፣ ግብይትና እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ መላክ ዘርፎች የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን አገራት ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ መጠቀምም በፕሮጀክቱ የተያዙ ተግባራት ናቸው ብለዋል። በአውሮፓ ህብረት ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ሚስተር ዶሚኒክ ዳቮክስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የቡና ልማት ስራ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል። ህብረቱ ከሚያከናውናቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ይህ ፕሮጀክት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ወደውጭ ከምትልከው የቡና ምርት 42 በመቶ የሚሆነው ወደአውሮፓ አገራት የሚላክ በመሆኑ የቡና ልማትን መደገፍ ለህብረቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ከኢትዮጵያ ቡና ገዢዎች ትልቁን ድርሻ የሚይዙ አገራት ናቸው።