ቀጥታ፡

የአገር በቀል እውቀት ትሩፋትና የተዘነጋው የስራ እድል

ነሀሴ 30/2011 የአርሲ ነገሌ ከተማ ነዋሪው አቶ ዘውዱ አስፈራቸው ኑሯቸውን የመሰረቱት በአካባቢው በባህላዊ መንገድ በሚመረተው አረቄ ንግድና ቀማሽነት ስራ ላይ ነው። ይህንን በባህላዊ መንገድ የሚመረት አረቄ ካቲካላ/ ለገበያ በማቅረብ 10ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን በተጨማሪም ከጀሪካን ወደ ጠርሙስ እየሳቡ በማውጣት ቀማሽ ‘ባለሙያ’ ጭምር መሆናቸውንም ይናገራሉ። የአረቄን “ባህላዊ ደረጃ” በቅምሻ በመለየትና በአቅራቢነት ባለፉት ዓመታት ኑሯቸውን የመሩበት ዘርፍ ነው ። በአርሲ ነገሌ ልክ እንደእርሳቸው አረቄ በመቅመስና የገበያውን ዋጋ በመወሰን የሚተዳደሩ 300 ያህል ባለሙያዎች አሉ።በሳምንቱ ውስጥ ልዩ የገበያ ቀናት በሆኑት ሰኞ ፣ ረቡዕና ዓርብ የሚቀርበውን አረቄ በመቅመስ “ባህላዊ ደረጃና ዋጋ” ይወስናሉ። እነዚህ ሽያጮች ሲካሄዱ እንደ አቶ ዘውዱ ያሉ ቀማሾች የአረቄውን ጥራትና ጥንካሬ መወሰን ይጠበቅባቸዋል። እየቀመሱ በመትፋት ጥራቱ አንደኛ ነው፣ ሁለተኛ ደረጃ ነው፣ደካማ ነው ይላሉ። አቶ ዘውዱ እንደሚሉት፤ የአረቄውን መልክ በማየትና በመቅመስ የጥራት መጠኑን ያውቁታል።የሚቀምሱትን ወደ ውስጥ ሳያስገቡ ስለሚተፉት “በጤንነቴ ላይ የጎላ ጉዳት ያስከተለበት አጋጣሚ የለም” ይላሉ። እርሳቸውን ጨምሮ እነዚህ ‘ባለሙያዎች’ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገበያውን ዋጋ የመወሰን አቅም እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ዘውዱ ገበያው ለአካባቢው ህዝብ እንደ አንድ ትልቅ ፋብሪካ መተዳደሪያው መሆኑንም ያመለክታሉ። የራስወርቅ አድማሱ እና ኢዛናአ አምደወርቅ በ2010 በማህበራዊ ኢኮኖሚ አተያይ ባደረጉት ጥናት እንዳመለከቱት በአርሲ ነገሌ የገበያ ትስስር ውስጥ ቀማሾች፣ አሻሻጮች፣ ገበያ ዋጋ ተደራዳሪዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። እነዚህ የገበያ ትስስሮች የብዙ ሰዎችን ኑሮ ለመምራት የሚያስችሉ ናቸው ። ጥናቱ እንዳመለከተው ከሆነ አርሲ ነገሌ የሚገኙ የጠባቂዎችና ደላሎች ማህበር ከሚያገኘው ገቢ ረዳት የሌላቸውን ልጆች ይደግፋል ። ትምህርታቸውን እንዲከታተሉም ያደርጋል። ባህርዳር ዩኒቨርስቲ እ.ኤ.አ 2012 ባዘጋጀው ሲምፖዚየም የቀረበ ጥናት እንደሚያመለክተው ፤በአገር በቀል እውቀት የሚመረቱት አብዛኛዎቹ ምግብና መጠጦች በርካታ ሰዎች ኑሮዋቸውን ለመምራት የሚያስችላቸው ገቢ ያስገኝላቸዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአምቦ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ ታሪኩ ሁንዱማ በዚሁ ጥናት ምንጭ ጠቅሰው እንደገለጹት፤ በአርሲ ነገሌ ከተማ ብቻ በአረቄ ገበያ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሆኑት 87 ነጥብ 3 በመቶዎቹ ናቸው። የምግብ፣ መጠጥና የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የመጠጥ ፕሮሰሲንግ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ከፍያለው እንደሚሉት በባህላዊ መንገድ የሚወጡት አረቄና ሌሎች መጠጦች ለበርካታ ሰዎች የኑሮ ዋስትና ናቸው። “ይህ ባህላዊ መጠጥ በተሻለ መንገድ ቢመረትና ታሽጎ ቢወጣ የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል ። የውጭ ምንዛሪም ያስገኝ ነበር። ነገር ግን ክትትልና ድጋፍ አይደረግለትም”ብለዋል። እስከ አሁን ድረስ ድጋፍና ክትትል ላለመደረጉ በምክንያትነት የቀረበው የሰው ሃይል እጥረትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ውሱንነት ሲሆን በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በአርሲ ነገሌ አካባቢ በየአንዳንዱ ቤት በስድስት ቀን ውስጥ 150 ሊትር አረቄ ይመረታል። በደብረ ብርሃን፣ በሰላሌና በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ለብዙዎች የስራ እድል የፈጠረው የአገር በቀል እውቀት ስራዎችን እውቅና ሰጥቶ በኢንተርፕሬነርነት አደራጅቶ በንግድ ሰንሰለት በማካተትና በህጋዊ መንገድ ስራዎችን ለማከናወን የክትትልም ሆነ የድጋፍ ችግር መኖሩን ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚያመለክቱት። ከዚህ ይልቅ በግልጽ ገበያ በሁሉም የእድሜ ደረጃ ላይ ሰዎች እንደሚገበያዩም ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ሀገሪቷ ካወጣችው ህግ ጋር ይቃረናል። በአርሲ ነገሌ ገበያው በየቀኑ በአማካይ ከ20 እስከ 30 አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች የባህል አረቄ ጭነው ወደተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደሚጓጓዝ አቶ ዘውዱ ተናግረዋል። በየራስወርቅ እና ኢዛና ጥናት ላይ እንደተመለከተ ጥናቱን ባከናወኑበት ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ነጋዴዎች ከገበያው አረቄ በጀሪካን በመሰብሰብ ከ3 እስካ 4 አይሱዙ ጭነው ይወጣሉ። ከዚህ በተለየ መልኩ ደግሞ እንዳቅማቸው እየሰበሰቡ በአውቶቡስም ጭነው ይወጣሉ። ይህ አሁን ካለው ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው። ገበያው እያደገ መጥቷል። ሌላው አረቄ ቀማሽ “ባለሙያ”ወጣት ደጀኔ ወልደማርያም በሰጠው አስተያየት፤ ለገበያ የሚቀርበውን አረቄ በመቅመስ የሚተዳደር ቢሆንም ገበያወ ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር በውሃ እጥረት ምክንያት መቀዛቀዝ እየታየበት ይገኛል። ከአካባቢው በፊት በቀን በአማካይ እስከ 20 መኪና አረቄ ተጭኖ ሲወጣ ነበር ።አሁን ግን ቀንሶ ወደ 15 አይሱዙ ዝቅ ማለቱንም አቶ ደጀኔ ተናግሯል። በአርሲ ነገሌ ከተማ አስተዳደር የገበያ ልማት የስራ ሒደት ዋና ሃላፊ አቶ ከድር ዋቆ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ሳምንቱን ሙሉ የአረቄ ግብይት ይካሔዳል ። በሶስቱ ዋነኛ የአረቄ የገበያ ቀናት በየእለቱ በአማካይ 30 አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች አረቄ ጭነው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ይጓዛሉ። ይህን ሀሳብ በተመለከተ የአረቄ ጫኝ ሰራተኞች የተለየ አመለካከት አላቸው። እንደነርሱ እምነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው በተከሰተ የውሃ እጥረት በአይሱዙ ተጭኖ የሚወጣው የአረቄ ቀንሷል።ይህም ቢሆን ከፍተኛ የገበያ ፍላጎትና የገንዘብ ዝውውር መኖሩን ያመላክታል። አቶ ከድር እንደሚናገሩት፤ የአበሻ አረቄውን የጥራት ደረጃና ዋጋ የሚወስኑ ቀማሾች በማህበር የተደራጁ፣ በነጋዴዎች የተመረጡና በገበያው ረጅም ጊዜ የሰሩ ናቸው። የተቀመሰው አረቄ ለአንድ ባለ 25 ሊትር ጀሪካን ከ150 እስከ 800 ብር የሚያወጣ ደረጃ ይሰጠዋል። በአርሲ ነገሌ ከተማ “አረቄ የማይወጣበት ቤት የለም” ያሉት ዋና የስራ ሂደት ሃላፊው፤ ምክንያቱ ደግሞ ከአረቄው ከሚገኘው ገቢ ባሻገርአተላው ወይም ዝቃጩ ለእንስሳት እርባታ አገልግሎት በመዋል ሌላ የገቢ ምንጭ ሆኖ ስለሚያገለገል እንደሆነም ጠቁመዋል። የምግብ፣ መጠጥና የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የመጠጥ ፕሮሰሲንግ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ እንደሚናገሩት በተለያዩ አካባቢዎች በብዛት ይመረታል። በአገሪቷም ሆነ በአርሲ ነገሌ ከተማ ከዓመት ዓመት የማያቋርጥ ሰፊ የባህላዊ አረቄ ግብይት እየተካሔደ ቢሆንም የፈጠረው የስራ ዕድል ፣ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ፣ የጤና ተጽዕኖ እንዳለውና ከቀረጥ ለከተማው የሚያበረክተው ገቢ በተመለከተ የተካሄደ ጥናትና የተደራጀ መረጃ አለመኖሩን ከሃላፊዎቹ ማብራሪያ ለመረዳት ይቻላል። የሀገር በቀል እውቀት ውጤት የሆኑት ምርቶች በገበያ ያላቸው ድርሻ፣ የገበያው ትስስር ታስቦ ወደ ተሻለ የአመራረት ደረጃ በማድረስ ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተለይም ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ከዩኒቨርሲቲ ባሻገር የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ያለማድረጋቸውንና ለኢንተርፕሪነርሺፕም ባለማድረሳቸው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊኖር የሚችለውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ማስቀረቱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም