የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 17 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 17 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዘገበ
ነሐሴ 29 /2011 የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 17 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገለፀ። ግሽበቱ ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በዋና ዋና እህል ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ለአጠቃላይ ግሽበቱ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ነው። ይኸው ጭማሪ ያለማቋረጥ መቀጠሉንም ኤጀንሲው አመልክቷል። ለምግብነት ተፈላጊ የሆኑ አንዳንድ የአትክልት ዓይነቶች በተለይም ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት በአንድ ወር ውስጥ የተጋነነ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። ይህም የዋጋ ግሽበቱ ከፍ እንዲል እንዳደረገው ነው የኤጀንሲው መግለጫ የጠቆመው። ሆኖም በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች የስንዴ፣ ሩዝና ዳቦ ዋጋ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑንም አመልክቷል። የልብስና መጫሚያ፣ የቤት ኪራይ፣ የህክምና፣ የቤት መስሪያ እቃዎች፣ ትራንስፖርት፣ ከሰል እና የማገዶ እንጨት በወሩ ውስጥ ጭማሪ አሳይተዋል።