ቀጥታ፡

የመድሃኒት አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በ150 የጤና ተቋማት የሙከራ ትግበራ ይጀመራል

ነሀሴ 29/2011 በመላ ሀገሪቱ የመድሃኒት አቅርቦትና ተደራሽነትን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ በ150 የመንግስት የጤና ተቋማት በቀጣዩ አመት የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ተናገሩ፡ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በተጠናቀው የበጀት አመት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ማሰራጨቱን አስታውቋል፡፡ ኤጀንሲ ያዘጋጀው 3ኛው የመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት አመታዊ የውይይት መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደተናገሩት የሙከራ ትግበራው ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት በመድሃኒት አቅርቦት ችግር የሚደርስበትን እንግልት በማስቀረት ተጠያቂነት ያለው የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት ያግዛል ብለዋል፡፡ ለሙከራ ትግበራው በተመረጡት ጤና ተቋማት ውስጥ ኤጀንሲው በሚመድባቸው ባለሙያዎች አማካኝነት በየቀኑ ከሚመጡ ታካሚዎች ምን ያህሉ መድሃኒት ሳያገኙ እንደተመለሱ መረጃ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡ ከሚሰበሰበው መረጃ በመነሳትም የመድሃኒት እጥረቱ ከማከማቻ መጋዘኖችና ከኤጀንሲው ወይም ከሆስፒታሎች መሆኑ በማረጋገጥ ተጠያቂነት ያለው የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት አመት በአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመው አሰራሩ የመድሃኒት ብክነትን በማስቀረት ስርቆትና ህገ-ወጥ ዝውውርን በመቆጣጠር ፍትሃዊ የመድሃኒት ስርጭት እንዲሰፍን ያስችላል፡፡ መንግስት ባለፉት ዓመታት ለመድሃኒትና ለህክምና መሳሪያዎች ግዢ በዓመት በአማካይ የሚመድበው የውጪ ምንዛሬ መጠን ከ27 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም ነበር ያሉት ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት ግን በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በመድሃኒት ግዢና ጨረታ የሚታየውን የአሰራር መጓተትና ረጅም ቀናት ለማስቀረት በተደረገው ጥረት አንድ ግዢና ጨረታ የሚወስደውን የአንድ አመት ጊዜ ወደ ስድስት ወራት ማሳጠር ተችሏል ብለዋል፡፡ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ 80 በመቶ የሚሆነው የመድሃኒት ግዢ በማእቀፍ ግዢ እንዲከናወን ከኤጀንሲው ጋር ስምምነት ተደርሷል ያሉት ዶክተር አሚር በዚህም በዓመት 300 ሚሊዮን ብር ብክነት በማዳን ለመቆጠብ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ የመድሃኒት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብረሃም በበኩላቸው ኤጀንሲው በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችና የህክምና ገልገያ መሳሪያዎች ግዢና ስርጭት ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡ የምክክር መድረኩ በመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ችግሮችን በመለየት ተጠቃሚዎች ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎትን የሚያገኙበትን ሁኔታ ከአጋር አካላት ለማመቻቸት ያለመ ነው ብለዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ የፌደራል የጤና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ፣ የሁሉም ክልሎች የጤና ቢሮ ሃላፊዎች፤ የመድሃኒት አስመጭና የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ አጋር አካላት ተሳታፊ ናቸው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም