በሶማሌ ክልል የተሻለ ሰላም መፍጠር መቻሉን የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የተሻለ ሰላም መፍጠር መቻሉን የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ
አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2011 ኅብረተሰቡና ከመንግስት በትብብር በመስራታቸው ሶማሌ ክልል የተሻለ ሰላም መፍጠር መቻላቸውን የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪና የሃይማኖት አባቶች ገለጹ። በአሁኑ ወቅት የክልሉ ነዋሪዎች ''በፊትም ወደምንታወቅበት ተከባበሮ፣ ተቻችሎና ተባብሮ የመኖር እሴታችን ተመልሰናል'' ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ። በሶማሌ ክልል የደብረ መዊ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ሊቀ አዕላፍ ተስፋዬ ደጀኔ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በ2010 ዓ.ም የተፈጸመው አሰቃቂና አስነዋሪ ድርጊት የጥቂት ግለሰቦች ሴራ ነው። በሶማሌ ክልል የሰላም አየር መተንፈስ የማይቻልበት ጊዜ እንደነበርም አስታውሰዋል። ''በክልሉ የ 33 ዓመት ቆይታዬ እንዳለፈው ዓመት አስቸጋሪና ስርዓት አልበኝነት የነገሰበት የመከራ ዘመን ገጥሞኝ አያውቅም'' ይላሉ። የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሃመድ ሸቅለኔ ማንነታቸው በውል የማይታወቁ ቡድኖች በከፍተኛ አመራሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው በዜጎች ላይ አደጋ ይፈጥሩ እንደነበር ገልፀዋል። ይሁን እንጂ አዲሱ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሙስጠፊ መሀመድ ዑመር ወደሃላፊነት ከመጡ በኋላ ሁሉም ነገር መስመር መያዝ መጀመሩንና የክልሉ ሰላም መሻሻሉን ጠቁመዋል። የሶማሌ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልቃድር በሽር በክልሉ የተፈጸመው ድርጊት "ከተለያዩ ብሄሮች የተወለዱ የአንድ እናት ልጆች በጥርጣሬ እንዲተያዩ ያደረገ" ሲሉ አስታውሰውታል። ''ችግሩ በተከሰተበት ወቅት የሌላ ብሄር ተወላጆች ብቻ ሳይሆን እኛም በሰቀቀን እንድንኖር ተገደናል፤ ወደፊት እንዳይደገም ሁሉም በጥንቃቄ መስራት ይጠበቅበታል'' ብለዋል። በኅብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ትብብር የሶማሌ ክልል ቀድሞ ወደምትታወቅበት ሰላሟ በመመለስ የሁሉም መኖሪያ መሆኗን ማሳየቷን ሊቀ አዕላፍ ተስፋዬ ደጀኔ ገልጸዋል። ድርጊቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ቢያለፍም በህዝብና በመንግስት ትብብር ቤተ ክርስቲያናት እየተሰሩ ታቦተ ህጉ ወደ መንበረ ክብሩ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል። በእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና የመሰብሰቢያ አዳራሾች ፈንጂ ይቀበር እንደነበር የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ መሀመድ፤ ''ችግሩን ከመሰረቱ ለማጥፋት ሁሉም መተባበር ይገባዋል'' ብለዋል። በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች ቤተ ክርስቲያን ሲገነባም ሆነ መስጂድ ሲሰራ ክርስቲያንና ሙስሊም ብለው ሳይለያዩ በጋራ የመስራት የካበተ ልምድ ያላቸው መሆናቸው ይታወቃል።