የደቡብ አፍሪካ መንግስት በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት እንዲያስጠብቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ

107
ነሀሴ 29/2011 የደቡብ አፍሪካ መንግስት በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት እንዲያስጠብቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። ሚኒስቴሩ በየደረጃው የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ባለስልጣናት ጠንካራ ክትትል በማድረግ በውጭ ዜጎች ላይ በተፈጸመው ድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉና ለህግ እንዲያቀርቡም ጠይቋል። ሚኒስቴሩ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዜጎችን ኢላማ ባደረገ መልኩ የተፈጸመውን ጥቃትና የንብረት ዝርፊያ በፅኑ አውግዟል። የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲርል ራማፎሳ ድርጊቱን በማውገዝ በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንደሚያቀርቡ የገቡት ቃል አበረታች እንደሆ ሚኒስቴሩ ገልጿል። ፕሬዚዳንቱ በገቡት ቃል መሰረትም በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርቡ የሚኒስቴሩ እምነት መሆኑ ተገልጿል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ ከሚመለከታቸው የአገሪቱ ባለስልጣናትና ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመሆን ሁኔታውን ለማረጋጋት በቅርበትና በትብብር እየሰራ እንደሆነ ተጠቁሟል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ኤምባሲው የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም